
ደሴ: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለታላቅ ሕዝብ ታላላቅ ተቋማት ያስፈልጉታል፤ ለታላቅ ሕዝብ ታላላቅ ልማቶች ይገቡታል። ታላላቅ ተቋማት ታላቅ ሀገርን ይገነባሉ፣ የሕዝብን ጥቅም ያስከብራሉ፣ ድኅነትን ታሪክ ያደርጋሉ፣ ኃላቀርነትን ያሻግራሉ፣ ከዘመኑ ጋር ያራምዳሉ፣ አለፍ ሲልም ከዘመን ያስቀድማሉ፣ ለልጅ ልጅ ታላቅ ጥሪትን ለማቆዬት ይረዳሉ።
ታላላቅ ሐሳቦች በየዘመናቱ ይፈጠራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከዘመን ቀድመው ይፈጠራሉ። አንዳንዶቹ ከዘመኑ ጋር ተስማምተው ይመጣሉ፣ ከዘመን ቀድመው የሚፈጠሩትም፣ ከዘመኑ ጋር ተስማምተው የሚመጡትም ከሀሳብነት አልፈው፣ ከተስፋና ራዕይ ተሻግረው እውን በኾኑ ጊዜ ሕዝብና ሀገርን ታላቅ ያደርጋሉ።
ዳሩ ብዙ ጊዜ ታላላቅ ሀሳቦች ከተስፋነት ሳያልፉ፣ ከሕልም ሳይሻገሩ ባክነው ይቀራሉ። ታላላቅ ሐሳቦቻቸውን እውን ያደረጉ፣ ተስፋውን ዳቦ እንዲኾን የተጉ አልፎላቸዋል፣ በታላላቅ ሐሳቦቻቸው ታላላቅ ተቋሞቻቸውን ገንብተው ሕዝባቸውን ጠቅመዋል፣ ሀገራቸውን አኩርተዋል።
አንዳንዶቹ ደግሞ ታላላቅ ሐሳቦችን አስበው፣ ታላቅ ሕልም ሰንቀው ሐሳባቸውን ሳይቋጩት ያልፋሉ፣ ሕልማቸውን ሳይኖሩት ይቀራሉ። ሀገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ታላላቅ ሐሳቦችን በጋራ መተግበር፣ ከተስፋነት አሻግሮ በተግባር መኖር ሲቻል ሕዝብ ይከበራል፣ ሀገር ይኮራል። የሕዝብን ታላቅነት በሚያስጠብቁ ፣የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ፣ የጋራ ልማትን እና እድገትን በሚያመጡ መልካም ሀሳቦች ላይ በጋራ መሥራት ፍሬው በሕዝብ ሕይወት ላይ ይታያል።
ሀገራት ያደጉት ለሕዝብ ጠቃሚ የኾኑ ሀሳቦችን ተቋም አድርገው በመገንባታቸው፣ በተቋሞቻቸውም ሐሳቦቻቸውን በመተግበራቸው እና ለአንድ ሕዝብ ጥቅም በጋራ በመሥራታቸው ነው።
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ታላላቅ ሐሳቦች የፈጠሩት ታላቅ ተቋም ነው። ተቋሙ ለአማራ ክልል አለፍ ሲልም ኢትዮጵያን በልማት የተሻለ የማድረግ አቅም ያለው ነው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ ታላላቅ ሥራዎችን ለመሥራት የተቋቋመው ይህ ታላቅ ተቋም ታላቅ ተስፋ የተጣለበት፣ ተስፋውን እና ሕልሙን ለማሳካት እየተጓዘ ያለ ተቋም ነው። ተቋሙ በዓመት በሺዎች የሚቆጠር ቶን ብረቶችን ማቅለጥ የሚችል፣ ከውጭ የሚመጡ እና በውጭ ባለሙያዎች የሚገጣጠሙ ቴክኖሎጂዎችን በራስ ባለሙያ፣ በራስ አቅም፣ በራስ ሀገር መሥራት የሚችል ነው።
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ እየተገነቡ ያሉ ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚገጣጥም፣ በኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት የሚችል፣ የሀገርን ልጆች አቅም የሚያሳድግም ነው። ተቋሙ አቅሙን እያሳደገ ሲሄድ በሀገር ውስጥ አይሞከሩም የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ይችላል። በውጭ ባለሙያዎች ተይዞ የነበረውን እውቀት በሀገር ልጆች የያዘ እና አቅሙን እያሳደገ ያላ ተቋም ነው።
በአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ የኮምቦልቻ እርሻ መሳሪያ ፋብሪካ የምርት እቅድና ክትትል ኀላፊ ናሆም ዓለምሰገድ ተቋሙ የፋብሪካ ሥራውን በራሱ አቅም ገንብቶ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። ለወትሮው ሌሎች ተቋማት የፋብሪካ ግንባታቸውን በሌሎች አሠርተው ወደ ምርት ይገባሉ፣ የአማራ ብረታብረት ግን በራሱ አቅም፣ በራሱ የሰው ኀይል ፋብሪካውን ግንብቶ ነው ወደ ሥራ የገባው።
ፋብሪካው የተሠራባቸው ጥሬ እቃዎች በራሱ ባለሙያዎች የተቀረፁና የተሠሩም ናቸው። ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ያልተለመደ ዓይነት መኾኑን ያነሱት ናሆም ከአሁን በፊት ማሽነሪዎች ከውጭ የሚመጡ ማሽኖችን ራሳቸው መያዛቸውን ተናግረዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት በሀገር ላይ የሚገነቡ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን ለማምረት አቅም ይዘው መነሳታቸውንም ገልጸዋል።
በፋብሪካዎቻቸው ላይ ብልሽት ሲገጥም ከውጭ ባለሙያዎች እና ፍብሪካዎች ጋር ሲሠሩ ለነበሩ ሁሉ እነርሱ የጀርባ አጥንት ኾነው መምጣታቸውንም አስታውቀዋል። በውጭ ባለሙያዎች እና ፋብሪካዎች ይሠሩ የነበሩትን ሁሉ በራሳቸው አቅም እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።
በሀገር ውስጥ መሥራት በመቻላቸው ሥራን ቀልጣፋ በማድረግና የፋብሪካዎችን ወጪ በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። ማሽኖችን እያመረቱ ለፋብሪካዎች እንደሚሸጡም አስታውቀዋል። በፋብሪካው የፋብሪካ ሸዶችን፣ የነዳጅ ታንከርን፣ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽንን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ሸዶችን አምርተው መስጠታቸውን እና አሁንም እየሠጡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የኮምቦልቻ እርሻ መሣሪያ ፋብሪካ ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው በግብርናው ዘርፍ ያሉ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ነው ያሉት ኀላፊው ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በማስቀረት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ለማምረት እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ግብዓት የሚኾኑ ዘመናዊ ምርቶችን ለማምረት እየሠራን ነውም ብለዋል። ፋብሪካው በሀገር ውስጥ ያልተለመዱ ሥራዎችን በመሥራት የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተመርቀው ሥራ ላልያዙ ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል።
ፋብሪካው ለ140 ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩንም አመላክተዋል። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ከአንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥር እንደሚችልም ተናግረዋል። ፋብሪካው ጥሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት እና ባለሙያዎቹ ጥሩ እውቀት የሚቀስሙበት መኾኑንም ገልጸዋል።
በቅርቡ ያስገቧቸው ማሽነሪዎች የተሻሉ ምርቶችን እንደሚያመርቱም ተናግረዋል። ሰላም ለኢንዱስትሪዎች ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ሰላም ካልኾነ ፋብሪካው የሚፈልጋቸውን ጥሬ እቃዎች ከሌላ ቦታ ማምጣት እና ያመረታቸውን ምርቶች መሸጥ እንደማይችል ነው ያብራሩት።
በወረራው ጦርነት ወቅት ፋብሪካው ጉዳት ደርሶበት እንደነበርም አስታውሰዋል። በጦርነቱ ምክንያት የጀመሯቸው ሥራዎች ተቋርጠው እንደነበርም ገልጸዋል። በጦርነቱ ምክንያት የጠፉ እና የተበላሹ ማሽነሪዎች እንደነበሩም ተናግረዋል።
የጠፉትን ማሽነሪዎች በራሳቸው አቅም እያመረቷቸው መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የማይቻሉትን ደግሞ በግዥ እያሟሉ መኾናቸውን ነው የነገሩን። ፋብሪካው ለክልሉና ለመላው ኢትዮጵያ ታላቅ አቅም መፍጠር የሚችል መኾኑንም አስረድተዋል።
ታላቅ ራዕይ ይዞ የተነሳው፣ ሐሳቦችን እየተገበረ ያለውና ሩቅ የሚጓዘው ተቋም ተስፋ ተጥሎበታል። ዘመኑን የዋጀና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ልማት እንዲኖርም ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የሕዝብ ጥቅም ለሚያስከብሩ፣ የጋራ እድገት ለሚያመጡ እና ሀገርን ለሚያኮሩ ሃሳቦች ድጋፍ ማድረግ የተገባ ነው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!