በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጠረጠሩ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

35

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች የሚነሱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ከመሰረቱ ለመፍታት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣ ግብረ-ኃይል ሕገ ወጦችንና ሙሰኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ለረጅም ጊዜ የተቀናጀ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል ይላል ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን የተላከው መግለጫ።

በመኾኑም ከተቋማቱ የተወጣጣውና ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ተገልጋዮች በመደበኛ የመንግሥት ሥርዓት የሚፈልጉትን የፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶችን በአፋጣኝና በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ የፈጠሯቸው የተንዛዙና እና የተወሳሰቡ አሠራሮች ዜጎችን ለከፋ እንግልት ከመዳረግ ባሻገር ላልተገባ ወጪ ሲዳርጉ ነበር ነዉ ያለው።

ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ በሙስና ተግባር መሰመራታቸውና የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ እንደነበር ተገልጿል። ግብረ-ኃይሉ ግለሰቦቹ በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኀላፊነት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ላልኾኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ በወንጀል ተከሰው የጉዞ ሰነዳቸው ለታገደባቸውና ሐሰተኛ የማንነት መገለጫ ላላቸው ሕገወጦች ጭምር የፓስፖርት፣ ሊሴፓሴና ቪዛ አየር በአየር በመሸጥ እና በማስተላለፍ፤ መንገደኞች በሌሉበት ጉዞ እንዳላቸው በማስመሰል እና የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደተዘዋወሩ የሚገለፅ ማሕተም በማዘጋጀት ተግባር ተሰማርተው ተገኝተዋል ብሏል።


በተጨማሪም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ተመልምለው ያለፉ እንደኾኑ በማስመሰል ግለሰቦች ባልተገባ መንገድ ለሥራ ወደ ተለያዩ የዓረብ ሀገራት እንዲወጡ በማድረግ እንዲሁም የሕጋዊ ግለሰብን ፓስፖርት ፎቶግራፍ በመቀየር ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንደተደረሰባቸው የግብረ-ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።

እነዚህ ወንጀለኞች ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የጥቅም ትስስር በመዘርጋት ሙስና ሲፈጽሙ ከመቆየታቸውም ባሻገር፤ ሐሰተኛ የማንነት መታወቂያዎችን በማዘጋጀት ተግባር ላይ ተሰማርተው ከነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ወንጀሉን ሲፈጽሙ እንደቆዩ ታውቋል።

ይህን ተከትሎም ግብረ-ኃይሉ ባደረገው ክትትል ከ200 በላይ የሚኾኑ በሕገወጥ መንገድ የተዘጋጁ ፓስፖርቶች እንዲመክኑ አድርጓል። የወንጀል ድርጊቱም መንግሥትን በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እንዳሳጣው በመግለጫው ተመልክቷል።

ግብረ -ኃይሉ በመግለጫው እንዳመለከተው በአዲስ አበባ ከተማ፤ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በወንጀሉ የተሳተፉ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሲያገለግሉ የነበሩ ከከፍተኛ አመራርነት እስከ ባለሙያ ያሉ 42 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡


በወንጀል ድርጊቱ ተሰማርተው ከተገኙና በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከልም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ግንበቶ አዋልሶን ጨምሮ ዘመድኩን ጌታቸው፣ ከድር ሰዒድ ስሩር፣ አስቻለው እዘዘው፣ አብዱላሂ አሊ መሀመድ (አብዱላሂ ጃርሶ)፣ ቴዎድሮስ ቦጋለ፣ ጌትነት አየለ፣ ጀማል ገዳ፣ ሙላት ደስታ፣ ጅላሎ በድሩ፣ ገነት ኃ/ማርያም፣ ደገፋ ቤኩማ ፣ ወንድይፍራው ሽመልስ ገ/ሰንበት እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል።

በተያዙት ተጠርጣሪዎች ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል። በግለሰቦቹ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ያላቸው ዜጎች ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

በኦፕሬሽኑ የተለያዩ ፓስፖርቶች፣ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎች፣ አየር በአየር የወጡ ሊሴ ፓሴዎችና የታተሙ ቪዛ ካርዶች በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤትና የሥራ ቦታ በተደረገ ብርበራ በኢግዝቢትነት መያዛቸውን ግብረ -ኃይሉ አመልክቷል።

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣው ግብረ -ኃይል በእንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር ዙሪያ የሚያካሂደውን ምርመራ፣ ክትትልና ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል ፤ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ማኅበረሰቡ ላሳየው የተለመደና ቀና ትብብር ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ነጻ የወጣንበትን ቀን አክብረናል” የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“ታላቁ የብረት ተስፋ”