“ነጻ የወጣንበትን ቀን አክብረናል” የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች

108

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለተሻገረ ጊዜ ከማንነታቸውና ከእምነታቸው በኀይል እንዲርቁ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ በማንነታቸው ተለይተው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ፤ አማራ ነን ስላሉ ምድራዊ መከራን ኹሉ የተቀበሉ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

በተለይ ደግሞ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰተውን የሰሜን ኢትዮጵያን ተደጋጋሚ ጦርነት ተከትሎ አማራ ነን ያሉ የአካባቢው ተወላጆች ውድ መሥዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ ታሪክ ነቅሰው መረጃ አጣቅሰው “አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም” ያሉ ሁሉ የደረሱበት አይታወቅም፡፡

በአካባቢው በተፈጠረ ተደጋጋሚ ጦርነት እና ግጭት እናቶች እና ሕጻናት ሳይቀሩ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ ሃብት እና ንብረታቸው በግፈኞች እንዲዘረፍ፤ እንደ ጥፋተኞች እንዲሳደዱ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ እነዚያ አስከፊ የመከራ እና የባርነት ዓመታት ዳግም ላይመለሱ ከተነቀሉ ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት አስቆጠርን ይላሉ፡፡

ዛሬ የነጻነታቸውን ቀን ሊያከብሩ እና ለነጻነታቸው መሥዋዕትነትን የተቀበሉትን ሊዘክሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአላማጣ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ “የታገልነው ግፈኞችን እንጂ ሕዝብን ስላልነበር አሸንፈናል” የሚሉት የከተማዋ ነዋሪዎች የጦርነትን አስከፊነት በለቅሶ ሳይኾን በተግባር መማር ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡

የአላማጣ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ሞገስ እያሱ የመጣንበት መንገድ ውጣ ውረድ የበዛበት ቢኾንም ለዘመናት የናፈቅነውን ነጻነት በማግኘታችን ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል፡፡ የራያ አማራ ሕዝብ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ቢኖሩትም ሁሉም ጥያቄዎቹ ከነጻነቱ በታች በመኾናቸው የነጻነቱን ቀን አስቀድሞ በደመቀ ኹኔታ አክብሯል ብለዋል፡፡

በቋንቋችን ተግባብተናል፣ በባሕላችን አጊጠናል፣ በማንነታችን ተከብረናል ፣ ተሰባስበናል ብለዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ እና አስተያየት ሰጭ አቶ ሞገስ ኃይሉ ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም አካባቢያችን ከግፈኞች አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነጻ የወጣበት ቀን ነው ብለውናል፡፡ ይህንን የሕዝብ ነጻነት ለማምጣት በርካቶች ውድ ዋጋ ከፍለዋል ያሉት አስተያየት ሰጭው ለተደረገልን ሁሉ ከራያ አማራ ሕዝብ ጎን ለቆሙ ሁሉ ምሥጋና አቅርበናል ነው ያሉት፡፡ ቀሪ የቤት ሥራዎች ቢኖሩንም በቅርብ እውን እንደሚኾኑ ተስፋ አለን ነው ያሉት፡፡

ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ወረራ ምክንያት ምጣኔ ሃብታዊ ፣ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉስቁልና የደረሰበት የራያ አማራ ሕዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ነጻ የወጣበት የነጻነት ቀን ነው ያሉን የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ አሥተዳደር ከንቲባ ኃይሉ አበራ ናቸው፡፡ የራያ አማራ ሕዝብ ላለፉት ዘመናት ጥያቄው ወደ ቀደመ እና እውነተኛ ማንነታችን እንመለስ ነበር ያሉት ከንቲባው የመጣንበት መንገድ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ቢኾንም ወደ ማንነታችን ተመልሰናል ብለዋል፡፡

በአላማጣ ከተማ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠር ሕዝብ የነጻነቱን ቀን ሊያከብር አደባባይ ወጥቶ እንደነበር የነገሩን ከንቲባ ኃይሉ ዓላማውም የነጻነት ቀኑን ማክበር እና ለነጻነቱ ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ መዘከር ነበር ብለዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ የተከበረው የነጻነት ቀን በሰላም መጠናቀቁንም ከንቲባው ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጉዛራን ቤተ መንግሥት ጥገና በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን
Next articleበሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጠረጠሩ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ።