“የጉዛራን ቤተ መንግሥት ጥገና በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን

56

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ እና እንዲያስጠብቅ ተጠይቋል።

ጉዛራ የጎንደር ዘመን ቀዳሚ መሥራች እንደኾኑ በሚነገርላቸው በአፄ ሰርፀ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1556 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ነው። ቤተ መንግሥቱ ከባሕር ወለል በላይ 200 ሜትር አማካኝ ከፍታ ካለው ማራኪ አምባ ላይ የተመሠረተ ነው።

በዙሪያው ያለውን የተንሰላሰለ መልክዓ ምድር ለማየት እንዲመች ተደርጎ የተሰራው የጉዛራ ቤተ መንግሥት በተለይም በአፄ ሚናስ ከተቆረቆረችው የእንፍራንዝ ከተማ በቅርብ እርቀት መገኘቱ ሳቢ አድርጎታል። በ10 ኪሎ ሜትር እርቀት ከጣና ሐይቅ አሻጋሪ መቀመጡ ደግሞ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም እንዲኖረው አድርጓል።

ለጎንደር የሥልጣኔ ዘመን ማሳያ ከሆኑት አብያተ መንግሥታት ውስጥ የጉዛራ ቤተ መንግሥት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የጉዛራ ቤተ መንግሥት የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሳል የኪነ ህንጻ ጥበብ ተደርጎም ይቆጠራል።

በወቅቱ የመጀመሪያው ባለሦስት ወለል ሕንጻ እንደኾነ የሚነገርለት የጉዛራ ቤተ መንግሥት በተለያዩ ዘመናት በደረሰበት ጉዳት የተለያዩ የጥገና ሥራዎች ቢደረግለትም ሙሉ በሙሉ ጥገና ባለማግኘቱ አሁንም ድረስ ከጉዳት ሳይላቀቅ ቆይቷል ተብሏል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም 35 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አማካኝነት የጥገና ሥራው እየተሠራ ይገኛል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንዳሉት ጥገናው በተያዘለት ጊዜ እና በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። የጥገና ሥራው የቅርሱን ታሪካዊ ዳራ ጠብቆ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና የማኅበረሰቡን ታሪክ፣ ባህል እና እሴት ከማስቀጠል ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የጥገና ሥራው በክልሉ በተፈጠረው ግጭቱ ምክንያት መጓተቱ እና ተጨማሪ ሥራዎች ቢኖሩበትም በ2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የቅርሱ ጥገና ሥራ በተቀመጠለት የጊዜ መርሐ ግብር እና በተመደበለት በጀት እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- በዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከመበላሸት መታደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ።
Next article“ነጻ የወጣንበትን ቀን አክብረናል” የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች