የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከመበላሸት መታደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ።

24

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015/16 ዓ.ም የመኸር እርሻ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተገልጿል። ከዚህም 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አግደው ሞላ “የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከመበላሸት መታደግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

አቶ አግደው በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ እስካሁን 478 ሺህ ሄክታሩ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ሰሊጥ፣ ባቄላ፣ ገብስ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ ቦለቄና ተልባ ከተሰበሰቡ ሰብሎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

በጥቅምት ወር ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል። አቶ አግደው አርሶ አደሮች ክረምቱን በሙሉ የለፋበትን ሰብል በወቅቱ በመሰብሰብ ከዝናብ ሊታደጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው ሰብሎች ለአጨዳ መድረሳቸውን ማረጋጋጥ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም በሰፋፊ ማሳዎች ላይ ሰብል የዘሩ ባለሃብት አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በሚሰበሰብበት ወቅት የማሳውን ሥፋት ግምት ውስጥ በማስገባት በቂ የሰው ኀይል ማሠማራት አለባቸው ብለዋል። የምግብ እና የሕክምና አገልግሎት በማቅረብ ሥራው በወቅቱ እንዲጠናቅ ማስቻል አለባቸውም ብለዋል። ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና ተማሪዎችንም ጭምር በመጠቀም በአግባቡ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

አቶ አግደው የምርት ጥራት ጉድለትን ሊያመጡ የሚችሉ ባዕድ ነገሮችን እንዳይጨመሩ፣ እርጥበት ጉዳት እንዳያደርስ እንዲኹም ለብክነት የሚጋብዙ ነገሮች እንዳይፈጠሩ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተለይ ዝናብ፣ጎርፍ፣ አሸዋ እና አይጥ ከመሳሰሉ ነገሮች ምርትን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የምናመርተው ምርት ለገበያ የሚቀርብ እና ለምግብነት የምንጠቀመው በመኾኑ ጥራቱ ተጠብቆ ሳይባክን ወደ ጎተራ መግባት አለበት ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ዝቅተኛ መኾን ምክንያቶች ተጠንተው ይቅረቡ” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
Next article“የጉዛራን ቤተ መንግሥት ጥገና በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን