“ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ዝቅተኛ መኾን ምክንያቶች ተጠንተው ይቅረቡ” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

43

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የትምህርት ሚኒስቴር ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ ምክንያት የኾኑ ችግሮችን በጥናት ለይቶ እንዲያቀርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።

በምክር ቤቱ የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ቀደም ሲል ሲሰጡ የነበሩ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቶች የተማሪዎችን ትክክለኛ ችሎታ ያሳዩ አልነበሩም ብለዋል።

የፈተና አሰጣጡን በመቀየር የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት በዘርፉ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ማሳያ መኾናቸውን ጠቁመው ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን ጠቅሰዋል። እየተካሄዱ ያሉ የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ መርሐ ግብሮችና የመምህራን አቅም ግንባታ ሥራዎችን ለአብነትም አንስተዋል።

በምክር ቤቱ የሰዉ ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሚኒስቴሩ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት መምጣት ሁሉንም ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

በመኾኑም የትምህርት ሚኒስቴር የማስተማርና ፈተና የማስፈተን ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደሚሠራ ተቋም ለተገኘው ውጤት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ተጠሪ ተቋማትና የትምህርቱ ዘርፍ ተዋንያን ለውጤቱ የነበራቸው ድርሻ ተለይቶ መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ማጣት ምክንያት የኾኑ ሌሎች ችግሮችም በጥናት ተለይተው ሊቀርቡ እንደሚገባም ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ጋር ተወያዩ።
Next articleየደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከመበላሸት መታደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ።