
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እውን በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል አስታውቋል::
የብዝኀ ሕይወትና ተፈጥሮ ሀብት ትክክለኛ አያያዝና ጥበቃ ላይ የተመሠረተና የተለያዩ ሥነ ምህዳሮች ተስማሚ የኾኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና በማፍለቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
የዞኑን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠንና ሕዝቡም በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እንዲሻሻል ማድረግ ተልዕኮው አድርጎም ይሠራል የደብረብርሀን ግብርና ምርምር ማዕከል።
ማዳቀል እና የመንዝ በግ ክብደት እንዲጨምር ማድረግ በእንሰሳት ዘርፉ ከሚሠሩ ሥራዎች ለአብነት የሚነሱ የምርምር ማዕከሉ ተግባራት ናቸው፡፡
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር አእምሮ በዛብህ (ዶ.ር ) የጥራጥሬ ሰብሎች የምርታማነት መጠን እንዲጨምር በድንች ፣ በስንዴ ፣ በማሽላ እና በባቄላ ላይ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የባቄላ ሰብል በቆርምድ በሽታ ተጠቅቶ ለአምስት ዓመት ገደማ አርሶ አደሮች ባቄላ ከማምረት የተቆጠቡባቸው ዓመታት መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የምርምር ተቋሙ ኖቨል የተሰኘ የምርምር ውጤት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ምርታማነቱ እንዲጨምር መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን በፀጥታ ችግር እንዲሁም በተለያዩ ተባዮች እየተፈተነ ባለበት ወቅት መስኖ ሥራ ዋነኛ አማራጭ መኾኑን የሚያነሱት ዳይሬክተሩ የመስኖ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ምርጥ ዘር እና የሙያ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮችም የበጋ መስኖ ሥራን በትኩረት በመሥራት ኢኮኖሚያቸውን እንዲያጎለብቱ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መኾናቸውን አጋርተውናል፡፡
ዘጋቢ ፡- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!