“ከሰላም በላይ ምንም የለም ፤ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን እንሠራለን” የደምበጫ ከተማ ነዋሪዎች

30

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኘው ደምበጫ ከተማ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሰላም እጦት ስትፈተን ቆይታለች። በተፈጠረው ችግርም በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱን ነዋሪዎች ለአሚኮ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከጥቅምት 4/2016 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ እና አካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። የተከሰተው ግጭት ቆሞ ነዋሪዎች ሰላም እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ወደ አካባቢው ገብተው ሲሠሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

ተቋርጦ የቆየው የከተማዋ እንቅስቃሴ ተመልሷል ፤ የተዘጉ ሱቆች እና ሌሎች የገበያ ቦታዎችም ከጥቅምት 3/2016 ዓ.ም ጀምሮ መከፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ለወራት ተስተጓጉሎ የቆየው የከተማዋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደገና እንዲጀመር የሚያስችል ሰላም በመምጣቱ መደሰታቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

“ከሰላም በላይ ምንም የለም፤ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን እንሠራለን” ሲሉ ነው ያነጋገርናቸው ነዋሪ የገለጹት። የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እና የመልካም አሥተዳደር እንቅፋቶች ተለቅመው እንዲቀረፉ ለማስቻል የሰከነ እና ሰላማዊ ትግል ማድረግ እንጂ ወደከፋ ጥፋት የሚያመራ አካሄድ መከተል አዋጭ አለመኾኑንም ተናግረዋል።

ነዋሪዎች የተገኘው ሰላም አስተማማኝ እና ዘላቂ እንዲኾን ሁሉም በባለቤትነት መንቀሳቀስ እና ለጥፋት የሚቀሰቅሱ አካላትን ጆሮ መንሳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወባን ለመከላከል የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል እርጭት ተካሄዷል” የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
Next article“ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ እየሠራን ነው” የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል