“ወባን ለመከላከል የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል እርጭት ተካሄዷል” የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

32

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሸታ ለመከላከል የአጎበር ስርጭት እና የወባ መከላከያ መድኃኒት ርጭት መካሄዱን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የክረምቱን መግባት እና መውጣት ተከትሎ በስፋት የሚከሰተው የወባ በሽታ በዚህ ዓመት ከሚጠበቀው በላይ የስርጭት አድማሱን አስፍቶ ኅብረተሰቡን ለከፋ የጤና ጉዳት እየዳረገ ይገኛል፡፡ አምራች በሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

በተለይም ወቅቱ የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ቢኾንም የወባ በሽታ አምራቹን ኃይል ከሥራው ውጭ አድርጎ ጤና ጣቢያ እንዲውል አድርጎታል፡፡

በሽታው ከሚያደርሰው የጤና እክል ባለፈ በኢኮኖሚው ላይም ከባድ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በወባ በሽታ ተጠቅተው በህክምና ጣቢያ የተገኙ አርሶ አደሮች ለአሚኮ እንዳሉት ወቅቱ የሥራ ጊዜ ቢኾንም የወባ በሽታ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ እንዳረረጋቸው ነው የነገሩን፡፡

ወባ ይይዘናል ብለው ጥንቃቄ እንዳላደረጉ የሚናገሩት ህሙማኑ ከራስ ተምሮ ሌላውንም ለመምከር መብቃታቸውን ነግረውናል፡፡

በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ ለአሚኮ እንዳሉት በዚህ ዓመት በክልሉ የወባ በሽታ በስፋት ተከስቶ ማኅበረሰቡን ለጤና እክል ዳርጓል፡፡

ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት የወባ በሽታ ስርጭት ከፍ ያለበትን ምክንያት ሲያብራሩ የአየር ሁኔታው ከወትሮው በተለየ ለወባ በሽታ መራባት አመች መኾኑ እና የኅብረተሰቡም ጥንቃቄ ከሚጠበቀው በታች መውረዱ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

አቶ አብርሃም ባለሙያዎች ወርደው እየደገፉ እና የጽዳት ሥራ እንዲሠራ በማድረግ ለወባ መራቢያ አመች የኾኑ ቦታዎችን የማጽዳት፣ የማዳፈን እና የማፋሰስ ሥራ ይሠራ የነበረ ቢኾንም አሁን ግን የክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ያንን ማድረግ እንዳላስቻላቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዳይሬክተሩ በተቻለ መጠን ወባ በሚያጠቃቸው 80 ወረዳዎች ላይ አጎበር እንዲሰራጭ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ አቶ አብርሃም በተለይም ችግሩ በስፋት በታየባቸው 190 ቀበሌዎች የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት መከናውኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ወባን ለመከላከል በመንግሥት በኩል የሚደረገው ቅድመ ጥንቃቄ እና ሕክምና እንዳለ ኾኖ ኅብረተሰቡ ግን ያለውን የዝናብ መውጣት እና መግባት እየተገነዘበ የአየር ሁኔታው ለትንኟ መራባት አመቺ በመኾኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የዓለም የዕይታ ቀንን አስመልክቶ የዓይን ህክምና አገልግሎት ሰጠ
Next article“ከሰላም በላይ ምንም የለም ፤ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን እንሠራለን” የደምበጫ ከተማ ነዋሪዎች