
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የዓለም የዕይታ ቀንን ”ትኩረት ለዓይናችን በሥራ ቦታችን“ በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የዓይን ጤና አገልግሎቶች በመስጠት እያከበረ ነው፡፡
ቢሮው በዓለም ለ23ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የዓለም ዕይታ ቀንን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና በጣና ሐይቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዕይታ ልኬታና የመነጽር ዕደላ በማድረግ አክብሯል፡፡
በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 6 በመቶ የዓይነ ስውርነት እና 3 ነጥብ 7 በመቶ የዕይታ መቀነስ ያለባቸው ወገኖች መኖራቸውን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ ፍስሐ አበባው ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ከምርመራ አገልግሎቱ በተጨማሪ የኅብረተሰቡን የዓይን ጤና አጠባበቅ ግንዛቤ የማሳደግ ትምህርት መሰጠቱን የተናገሩት አቶ ፍስሐ በምርመራ አገልግሎቱም ለ3 ሺህ ተማሪዎች፣ ለ150 መምህራን እና ለ400 የመንግሥት ሠራተኞች የዓይን ዕይታ ምርመራና አገልግሎትና መነጽር ዕደላ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
የዓይን ዕይታ ልኬታ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከኾኑት መካከል ተማሪ ግርማ ታደሰ እስከ 8ኛ ክፍል በሚማርበት ወቅት የባትሪ መብራት ይጠቀም ስለነበር በሂደት የዕይታ ችግር እንዳጋጠመው ገልጿል፡፡ በዕይታ ምርመራውም መነጽር ስለታዘዘለት ትምህርቱን ለመከታተል እንደሚስችለው ተናግሯል፡፡
በመንግሥት መስሪያ ቤት የሚሠሩት አቶ ክንዱ አበበ በበኩላቸው የሥራቸው ባህሪ ከኮምፒዩተር ጋር በብዛት ስለሚያገናኛቸው ለጥንቃቄ መነጽር የመጠቀም ልምድ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ በየሁለት ዓመቱም የዓይን ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ በሥራ ቦታ የዓይን ምርመራ በመደረጉም ለሠራተኛው የዓይን ጤናን ለመጠበቅ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ክንዱ ተናግረዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም መነጽር እጠቀማለሁ ፤ዛሬም ምርመራ ተደርጎልኝ መነጽር ታዝዞልኛል” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የሮም ምህረቴ ናቸው፡፡ ወይዘሮ የሮም “በሥራ ቦታ የዓይን ዕይታ ምርመራ መደረጉ የዓይናችን ደኅንነት ለመጠበቅ ያግዘናል” ነው ያሉት፡፡
በፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪምና የክፍሉ ኀላፊ ዶክተር ታደለ ግርማ የዓይን ዕይታ ችግር በአዋቂዎችና ሕጻናት የሚከሰት በሚል እንደሚፈረጅ ገልጸዋል፡፡
ኮምፒዩተርና ስልክ ሰፊ ጊዜ የሚጠቀሙ፣ ሕጻናትና ብረታ ብረት በያጆች ለችግሩ የበለጠ እንደሚጋለጡ ዶክተር ታደለ ገልጸዋል፡፡
የዓይን መቅላት፣ መቆጥቆጥና ራስ ምታት ሲከሰት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መመርመር እና መነጽርና ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግም ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡
የኮምፒዩተርና ሞባይልን ስክሪን ብርሃን መቀነስ እና ዓይንን በየተወሰነው ጊዜ መጨፈን ችግሩን ለመከላከል እንደሚመከር ጠቅሰዋል፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ፣ የቅርብና የርቀት ዕይታ ችግር ህክምና ካላገኘ ለዓይነ ስውርነት እንደሚዳርግም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!