
ጎንደር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም በሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሲቪክ ማኀበራት እና ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በጎንደር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
መንግሥት ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በመመለስ ለሰላሙ የድርሻውን እንዲወጣ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጎንደር ከተማን ጨምሮ አሁን ላይ በክልሉ የሰላም መደፍረስ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ተፈጥረዋል።
የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ “ሰላም ለሁሉም በሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪክ ማኀበራት እና ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በከተማው ወቅታዊ ሰላም ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ክልሉ ብሎም ከተማችን በተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል ብለዋል። ከተፈጠረው ግጭት በፍጥነት ወጥቶ ለሰላም እና ልማት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የውይይቱ ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት ለሕዝብ ሰላም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ለከተማዋ ሰላም የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የእርስ በእርስ ግጭት የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ አቅም የሚያሳጣ በመሆኑ የሰላም አማራጭን መጠቀም እንደሚገባ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
በመንግሥት በኩል መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ባለመሠራታቸው አሁን ለገጠመን ችግር ምክንያት ኾነዋልም ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መኖር፣ በየተቋማቱ የግል ጥቅማጥቅም የሚያሳዱ ግለሰቦች መበራከት፣ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች ችግሮች ወቅታዊ እና ተገቢ ምላሽ አለማግኘታቸው መንግሥት እና ሕዝብን ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎቹ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ፍላጎት ያለው ሕዝብ በመሆኑ ጥያቄዎቹን መንግሥት በአፋጣኝ መመለስ እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘጋቢ -ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!