
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንቦጭ አረም በጣና እና አካባቢው ላይ ከተከሰተ ከ10 ዓመት በላይ ኾኖታል። አረሙን ለመከላከል የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አበረታች ነው። ተቀናጅቶ በመሥራት በኩል ግን አሁንም ውስንነቶች እንዳሉ ይነሳል።
እንቦጭ ጣናን በማድረቅ በሰብልና በእንስሳት ልማት ላይም ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። ችግሩን ለመቅረፍም ኀብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር አረሙን ለመከላከል አስተባባሪ ተቋም ተቋቁሞለት እየተሠራ ነው።
በደቡብ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ ማሙሽ አማረ በዞኑ ከጣና ሐይቅ በሚዋሰኑ 3 ወረዳዎችና 10 ቀበሌዎች የተከሰተው እንቦጭ አረም ተለዋዋጭ ባህሪ ቢኖረውም ባለፉት ሁለት ዓመታት መቀነሱን ገልጸዋል። ለዚህም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠርና የመከላከሉ ሥራ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
አቶ ማሙሽ ኅብረተሰቡ እንቦጭን ከግል ማሣው ላይ ለማስወገድ ያለው ተሳትፎ አበረታች ነው ብለዋል። በወል መሬትና በሐይቁ ላይ የሚፈጠረውን አረም ለማስወገድ ግን ተጨማሪ ጥረት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ዉኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ.ር) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለእንቦጭ መከላከል የተሰጠው ትኩረት አናሳ መኾኑን አመላክተዋል። በማሽን የታገዘ የመከላከል ሥራ ለመሥራት የበጀት እጥረት መኖሩንም ነው የገለጹት። አረሙ እየተስፋፋ እስከ ባሕርዳር ከተማ መድረሱንም ተናግረዋል።
ከወቅታዊ የሠላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ የመፋዘዝ ኹኔታ መኖሩን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። አረሙ በውኃማ አካላት እና በአካባቢው ሥነ ምኅዳር ላይ የሚያስከትለውን ጥፋት በውል በመገንዘብ አረሙን ማጥፉት እንደሚገባም አንስተዋል። “ባለመዘናጋት እና በቅንጅት በመሥራት እንቦጭን መታገል ይገባል” ነው ያሉት።
“ሰላም ለሁሉም አይነት ሥራዎቻችን መሰረት ነው” ያሉት ሥራ አሥኪያጁ እንቦጭን ለማስወገድም ሰላምን ጠብቆ በትብብር ላይ የተመሰረተ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!