በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

26

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ችግር እንደኾነ የሚነገረው የኃይል አቅርቦት ነው። የኃይል አቅርቦት ችግር ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እና ሀገር ከኢንዱስትሪ ልታገኘው የሚገባትን ጥቅም ሲያሳጣ ቆይቷል።

በየከተሞች የሚስተዋለው የኃይል አቅርቦት እጥረት እና መቆራረጥ ባለሃብቶችን የሚያማርር ጉዳይ መኾኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። ባለሀብቶች በስፋት ኢንቨስት እንዳያደርጉም ያግዳቸዋል።

እንደ ሀገር እየገጠመ ያለውን እና ኢንዱስትሪዎችን በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ የከለከላቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር እየተገነባ ያለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብና ሌሎች ግድቦች ይፈቱታል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል።

በአማራ ክልል በበርካታ የኢንቨስትመንት ከተሞች የኃይል አቅርቦት ችግር በቀዳሚነት ይነሳል። ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ባለባት ኮምቦልቻ ከተማ የኃይል አቅቦት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ ነው ተብሏል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሀሽም ሰይድ ለኢንቨስትመንት አንደኛው ማነቆ የመሠረተ ልማት ችግር መኾኑን ነው የተናገሩት። መሠረተ ልማት ካልተሟላ ኢንቨስትመንት የተሟላ እንደማይኾንም ገልጸዋል።

በከተማዋ የተሻለ የመሠረተ ልማት አቅርቦት መኖሩንም ተናግረዋል። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳለው ሁሉ በከተማዋ የኃይል መቆራረጥ ችግር መኖሩን የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው ችግሩ ከፍተኛ የሚባል አለመኾኑን ግን አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የሰቭስቴሽን ግንባታ እየተከናወነ መኾኑንም አስታውቀዋል። በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሰቭስቴሽን 400 ኬቪ መኾኑንም አመላክተዋል።

ወደፊት በከተማዋ የኃይል አቅርቦት ችግር ይኖራል ተብሎ እንደማይታሰብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በባለሀብቶች የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ከተማ አሥተዳደሩ እየፈታ መኾኑንም አመላክተዋል።

በወረራው ወቅት ከተማዋ ጉዳት ደርሶባት እንደነበር ያስታወሱት ተወካይ ኀላፊው በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም ፋብሪካዎች ሥራ አቁመው እንደነበርም ተናግረዋል። በርካታ ፋብሪካዎችም ተዘርፈው እንደነበር ነው ያስታወሱት። ግብዓታቸው ፣ምርታቸው እና ማሽናቸው የተዘረፈባቸው ፋብሪካዎች እንደነበሩም ገልጸዋል። አካባቢው ከጦርነት ከወጣ በኋላም ወደ ሥራ ለመመለስ ብዙ ጊዜ ወስዶባቸው እንደነበርም ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም ፋብሪካዎች ችግር ደርሶባቸው ነበር። በርካታ ባለሀብቶች ግብዓቶችን ከውጭ አምጥተው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ተናግረዋል። ከነበረው ጉዳት ለማገገም የፌዴራል መንግሥትን ጨምቶ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው የተሠራው ሥራ ውጤት አምጥቶ ሥራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት።

ሁሉም ከጦርነቱ አገግመው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አመላክተዋል። በባለሀብቶች ጥንካሬ እና መንግሥት ባደረገው እገዛ ሁሉም ፋብሪካዎች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ማስቻሉን ነው የተናገሩት።

ጦርነቱ አሳድሮት የነበረው ጉዳትና ጫና ከፍተኛ እንደነበርም ተናግረዋል። የባለሀብቶች እና የመንግሥት ጥረት ባለሀብቶች ከጫና ወጥተው ሥራ እንዲጀምሩ እንዳደረጋቸው ነው የገለጹት። ይዘውት የነበረውን የሰው ኃይል ብዛት ይዘው እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኮምቦልቻ ከተማ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ምርት ገብተዋል” የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር
Next article“በባለብዙ ወገን መድረኮች አካታችነትን ማረጋገጥ ተገቢ ነዉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)