
ኮምቦልቻ፡ ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሚስተዋሉባቸው ከተሞች መካከል ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አንደኛዋ ናት።
አስፈላጊ የሚባሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያሟላችው ከተማዋ የበርካታ ባለሀብቶችን ቀልብ ትስባለች። ነግደው ማትረፍ የሚሹ ሁሉ ለሥራና ለትርፍ የተመቸችውን ከተማ ይመርጧታል።
ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የኾነችው ኮምቦልቻ በርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እየተከወኑባት ነው።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሀሽም ሰይድ ኮምቦልቻ ከተማ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የኾነች ከተማ መኾኗን ተናግረዋል። ከተማዋ የተሻለ መሠረተ ልማት ያላት መኾኗንም ገልጸዋል።
ከተማዋ ለወደብ ቅርብ መኾኗ እና የአየር ትራንስፖርት ያላት በመኾኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ ያደርጋታል ነው ያሉት። በከተማዋ የአውሮፕላን ጭነት (ካርጎ) ለማስጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። እየተገነባ ያለው የባቡር መስመርም ለከተማዋ ሌላኛው አማራጭ መኾኑን ነው የገለጹት። የከተማዋ ሕዝብ ሰላም ወዳድ፣ ሰላሙን ጠባቂ እና ሥራ ወዳድ መኾን ሌላኛው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጋት አጋጣሚ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በከተማዋ ከፍተኛ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ቅርንጫፎች መኖራቸው ከተማዋ ለኢንቨስትመንት የተመቸች እንድትኾን አድርጓታል ብለዋል።
በከተማዋ 865 ሄክታር መሬት ለ872 ፕሮጀክቶች መተላለፉንም ገልጸዋል። 129 አነሰተኛ ፣መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስታውቀዋል።
ወደ ሥራ የገቡት ኢንዱስትሪዎች 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ባስመዘገቡ ባለሀብቶች የተገነቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ወደ ሥራ የገቡት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለ6 ሺህ 561 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አንስተዋል። ወደሥራ የገቡት ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ መኾናቸውንም አመላክተዋል። 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 111 ፕሮጀክቶች የማልሚያ መሬት ወስደው በግንባታ ሂደት ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ሁሉም ወደ ሥራ በሚገቡ ጊዜ ከ10 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ነው የተባለው።
በከተማዋ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ በርካታ ባለሀብቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል። በኮምቦልቻ ከተማ ምርት ከጀመሩት ፈቃድ እስካወጡት ያሉት ባለሀብቶች 53 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ፈቃድ ያወጡትን ጨምሮ ሁሉም ወደ ሥራ ሲገቡ ከ121 ሺህ በላይ ወገኖች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ፈቃድ ያወጡ ባለሀብቶችን የቦታ ጥያቄ ለመመለስ ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከተማ አሥተዳደሩ 180 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት በመለየት 82 ሄክታር መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት 75 ባለሀብቶች ፈቃድ እንደሚያወጡ ይጠበቃል ያሉት ተወካይ ኀላፊው በሩብ ዓመቱ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 45 ባለሀብቶች ፈቃድ ማውጣታቸውንም ተናግረዋል።
የከተማዋን እድገት ታሳቢ በማድረግ የኀይል አቅርቦት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ባለሀብቶች ወደከተማዋ ቢመጡ ትርፋማ መኾን የሚያስችሉ እድሎች እንዳሏትም ገልጸዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ባለሀብቶችን ተቀብሎ በፍጥነት እንደሚያስተናግድም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
