
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ኹኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ በክልሉ የሰላም እጦት እንዲፈጠር ያደረጉ ምክንያቶች፣ ወቅታዊ የክልሉ የሰላም ኹኔታ እና የተፈጠሩ ችግሮች እንዲቀረፉ የተከናወኑ ሥራዎችን ተነስተዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመሥራት፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና የመሳሰሉ የቆዩ ጥያቄዎች እንዳሉት ቢሮ ኀላፊው በመግለጫቸው አንስተዋል። እነዚህን ጥያቄዎች የክልሉ መንግሥትም ተገንዝቦ መፈታት እንዲችሉ ትግል ሲያደርግ እንደቆየ እና አሁንም ለመፍትሔው እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ጥያቄዎቹ መሠረታዊ ናቸው፤ መፍትሔ የሚገኝላቸው ደግሞ በሂደት እንጂ በአንድ ጀንበር ሊኾን አይችልም ነው ያሉት።
የተፈጠረው የሰላም ችግር ወንድምን ከወንድሙ ጋር ያጋጨ ከመኾኑ ባለፈ በርካታ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ማስከተሉን ነው የገለጹት። እንዲህ አይነት ግጭት የአማራነትን ክብር የማይመጥን እና የትኛውንም አይነት የሕዝብ ጥያቄ የማይፈታ ነው ሲሉ ገልጸውታል። ይልቁንም በክልሉ እጅ ውስጥ ያሉ ዕድሎችን ጭምር የሚያሳጣ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
አቶ ደሳለኝ መንግሥትን በካርድ የመምረጥ እና የማውረድ ሥርዓትን መጠቀም ሲገባ ኃይልን በመጠቀም ወደ አውዳሚ አካሄድ መግባት ትርፉ ኪሳራ፣ ውጤቱም ሕዝብን አንገት ማስደፋት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አካሄድ ክልሉን፣ ሕዝቡን እና ሀገሩን ከሚወድ ዜጋ የሚመነጭ ሊኾን አይችልም ሲሉም ገልጸዋል።
የተፈጠረው የሰላም እጦት የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በማይፈልጉ አካላት ቅስቀሳ የተፈጠረ ስለመኾኑም ተደርሶበታል ብለዋል። ለሕዝብ የታገሉ በማስመሰል ክልሉን ወደባሰ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ማስገባት ፍጹም ስሕተት ነውም ብለዋል።
አቶ ደሳለኝ የእርስ በእርስ ግጭቱ በጥቂት አጥፊዎች ቅስቀሳ የተፈጠረ እንጂ ከሕዝብ ፍላጎት የመነጨ እንዳልኾነ በየአካባቢው በተደረጉ የማኅበረሰብ ውይይቶች ተገልጿል ብለዋል። ከዚህ ቀውስ መውጣት እንዳለብንም ማኅበረሰቡ እየገለጸ ይገኛል ብለዋል።
ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላም እና በኢትዮጵያዊ አብሮነት እንጂ በአፈሙዝ ሊኾን እንደማይችልም ማኅበረሰቡ በአጽንኦት እየተናገረ ስለመኾኑ አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው አንስተዋል።
የክልሉ መንግሥት ማኅበረሰቡን ያማረሩ በርካታ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች መኖራቸውን በማመን እንዲታረሙ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል። ሕዝቡም በአልባሌ ግጭት ውስጥ በመግባት የባሰ ቀውስ ከመፍጠር ተቆጥቦ ለተሻለ ክልላዊ ሰላም እና ልማት አጋዥ መኾን ይገባዋል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
በተፈጠረው ግጭት ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጥፋቶችን ያስከተለ ቢኾንም አሁን ላይ ግን በብዙ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ኾኗል ነው ያሉት። “ሁለት የታጠቀ አካል በአንድ ሀገር ውስጥ ሊኖር አይገባውም” ያሉት አቶ ደሳለኝ በመደማመጥ እና በመነጋገር ሁሉም የየድርሻውን ብቻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አቶ ደሳለኝ “ከሰላም ውጭ የሚመጡ ለውጦች ውጤታቸው እርስ በእርስ መጠፋፋት ነው” ሲሉም አሳስበዋል። በመኾኑም ለሕዝብ እና ለሀገር ጠቃሚ የሚኾን ለውጥ የሚፈልግ ሁሉ ከግጭት መራቅ እና ሰላማዊ መንገድን ብቻ መከተል አለበት ነው ያሉት።
“ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል አካል ሁሉ ለሕዝብ ሰላም እና ደህንነት አብዝቶ ሊጨነቅ ይገባል” ሲሉም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም የመንግሥት የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ማስተካከል፣ ሰላሙን ለመናድ ለሚነሱት ደግሞ ጆሮ መንሳት አለበት ሲሉ አንስተዋል።
አቶ ደሳለኝ የዜጎችን ሰላም ለማስከበር በመንግሥት በኩል ዋጋ እየተከፈለ መኾኑን ጠቅሰዋል። ክልሉ ወደተሟላ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ነው ብለዋል። ይህም በክልሉ ሕዝብ ላይ ተደቅኖ የነበረውን ጥፋት ያከሸፈ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ለሕዝብ ጥቅም ሲሉ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡም አቶ ደሳለኝ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!