
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በ2024 (እ.አ.አ) ከጣሊያኑ ክለብ ሮማ ጋር የነበራቸው የሦስት ዓመት ኮንትራት ውል የሚጠናቀቅ ይኾናል፡፡
ይህን ተከትሎም ክለቡ ሮማ ስለ ኮንትራት ማራዘሚያ ከሰሞኑ ጠይቋቸው ነበር፡፡ እሳቸውም “አይኾንም” ማለታቸውን ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
እየቆዩ የወጡት መረጃዎች እንዳመላከቱት ደግሞ ሰውየውን ከሳዑዲ አረቢያ ፕሮ ሊግ አንዱ ክለብ በ127 ሚሊዮን ዶላር ለመቅጠር ፍላጎት አሳይቷል እየተባለ ነው፡፡
የኾነው ኾኖ ፖርቱጋላዊው አወዛጋቢ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ጆሴ “አንድ ቀን የሳዑዲ አረቢያ ክለብን እንደማሰለጥን ውስጤ ይነግረኛል” ሲሉ መደመጣቸው ሰውየው ፊታቸውን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሳያዞሩ አልቀሩም የሚሉ የስፖርት ተንታኞችን ግምት የሚያጠንክር ይኾናል፡፡
ሰውየው የሚኾኑትን ሳይኾን በተቃራኒው ነው የሚናገሩ የሚሉት ተንታኞች ደግሞ ሞሪንሆ ከሳውዲ አረቢያ ክለቦች ይልቅ ከአውሮፓ ሀገራት ክለቦች አንዱን ማሰልጠን ሳይፈልጉ አይቀርም ሲሉ ግምት ማስቀመጣቸውን ስካይ ስፖርት አትቷል፡፡
ሞሪንሆ በሮማ ክለብ 119 ጨዋታዎች ያደረጉ ሲኾን 59 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት አጠናቀዋል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!