የኮሌራ ወረርሽኝን የተቆጣጠሩ አካባቢዎች ተሞክሮ ሊሰፋ እንደሚገባ የአማራ ከልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

25

ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ በሸታ ተከስቶ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ የተከሰተ በመኾኑ ክልሉ በሽታውን ለመቆጣጠር ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የበሽታው መነሻ ሊኾን የሚችለውን የግል እንዲሁም የአካባቢ ንጽህና ችግርን ኅብረተሰቡ ተረድቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሰፊ ጥረት ተድርጓል፡፡

በሽታው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ተለይተው ክትባት እንዲወስዱ የማድረግ ሥራም ተሠርቷል፡፡

በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የኮሌራ በሽታ መከሰቱ እንደታወቀ የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

በተለይም በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንደ ክልል ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ በየጤና ጣቢያዎች በልዩ ኹኔታ የህክምና ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ነግረውናል፡፡

አቶ አብርሃም በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሰፋ እንደሚችል በማሰብ ኅብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽህናውን እንዲጠብቅ ለማድረግ እና ክትባት ለመስጠት በተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቶበታል ይላሉ፡፡

አሁን ላይ የበሽታውን ስርጭት መጠን መቀነስ መቻሉንም አስገንዝበዋል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ላይም ማጥፋት የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው የነገሩን፡፡

አሚኮ ከዚህ በፊት በደቡብ ጎንደር ዞን የኮሌራ በሽታ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ የዞኑን ጤና መምሪያ ጠቅሶ ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዳይሬክተሩ በክልሉ በሽታው አስጊ ወደማይኾንበት ደረጃ እንደወረደ ገልጸዋል። ነገር ግን በምዕራብ ጎንደር መተማ፣ ደለጎ እና ባሕር ዳር ዙሪያ አንዳ፣ አቡነ ሃራ አካባቢ በሽታው አሁንም ስለመኖሩ ሪፖርት መደረጉን ነው የነገሩን፡፡

አቶ አብርሃም በሽታውን መቆጣጠር የቻሉ አካባቢዎች ተሞክሮ ወደሌሎችም ሰፍቶ በሽታውን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

የኮሌራ በሽታ በባሕሪው ተላላፊ በመኾኑ እንዳይሰፋ እና ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም ጥንቃቄ እንዲያደርግም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ደሴ የሰላም መምህርት፣ የፍቅር እመቤት”
Next articleበ2024 በጀርመን ለሚደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ማክሰኞ ምሽት ያደርጋሉ።