
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን ታስተምሪያለሽና ምሥጋና ይገባሻል፣ ፍቅር ትነግስብሻለችና ክብር ያንስብሻል ፣ሰውነት ይገለጥብሻልና እጅ ይነሳልሻል ፣ አንድነት ከፍ ይልብሻልና መከበር ያንስብሻል ፣ መወደድ ይኖርብሻልና ሞገሥ ይገባሻል፣ ሰላምን ትጠብቂያለሽ እና ደስታ ይመላብሻል። መልካሙ ሁሉ ይዘንብብሻል።
በተመቸም ባልተመቸም ዘመን ፍቅርን ታስተምራለች ፤ በከፋም በደግም ዘመን የመዋደድን ካባ ትደርባለች፣ የፍቅርን በትረ መንግሥት ጨብጣ ትኖራለች። ሰላም ጠፋ በተባለበት ዘመን የሰላም ዘውድ ጭና ትታያለች ፤ ሰላም ኮበለለ በተባለ ጊዜ የሰላም ካባ ደርባ ትዋባለች፣ የሰላም ጎዳናዎች ተዘጉ ሲባሉ ባማሩ የሰላም ጎዳናዎች በሚያማምሩ የፍቅር ሰረገላዎች ትረማመዳለች። ሰላምንም ታስተምራለች፣ ሰውነት በረከሰበት ዘመን የሰውነትን ልክ ትገልጣለች ፤ መዋደድ በማይታይበት ጊዜ መዋደድን ገንዘቧ ታደርጋለች ፤ የሚያስጨንቅ ዘመን በመጣ ጊዜ ጭንቀትን ታርቃለች።
እርሷ ፍቅር የሚፈስስባት የፍቅር ዥረት ናት ፤ እርሷ ሰላም የሚነግስባት የክብር ዙፋን ናት፣ እርሷ መዋደድ የሚጌጥባት ዘውድ ናት ፤ እርሷ አንድነት የሚጠብቅባት ቁልፍ ናት ፤ እርሷ አብሮነት የሚኖርባት ያማረ እልፍኝ ናት ፤ እርሷ ደስታ የማይነጥፍባት ምንጭ ናት፣ እርሷ ኢትዮጵያዊነት የሚገለጥባት መጽሐፍ ናት።
የናፈቀኝን አገኘሁት፣ የጓጓሁለትን ሰላም አየሁት፣ የሚተክዘውን ልቤን አረጋጋሁት ፣ የሚጨነቀው አዕምሮዬን በሰላም አስረሳሁት ፣ ደሴ ሰላምን አሳየችኝ፣ ሰላምን ሰጠችኝ ፣ የሰላምን አየር አስማገችኝ ፣ የፍቅሯን ካባ ደረበችኝ ፣ የመዋደዷን በትረ መንግሥት አስጨበጠችኝ ፣ ደሴ የሰላም መምህርት ፣ የፍቅር እመቤት ናት።
ጎተራው ቢትረፈረፍ ፣ ወይኑ ቢፈሰስ ፣ ወተት እንደ ወንዝ ውኃ ቢወርድ ፣ ልጆች ቢወለዱ ፣ ላሞች ቢረቡ ፣ አልማዝና ወርቅ የከበረው እንቁ ሁሉ ቢኖር ያለ ሰላም ምን ያደርጋል? በአልማዝ ባጌጠ ዙፋን ቢቀመጡ ፣ በእንቁ የተዋበ ዙፋን በአናት ላይ ቢያጠልቁ ፣ በወርቅ የተለበጠ ጎራዴ ቢታጠቁ ፣ እንደ ወላፈን የሚጋረፍ በትረ መንግሥት ቢጨብጡ ፣ እልፍ በግራ እልፍ በቀኝ፣ እልፍ በኋላ እልፍ በፊት እጅ የሚነሱ አገልጋዮች ቢበዙ፣ ጮማ ቢቆርጡ ፣ ወይን ቢጨልጡ ፣ በወርቅ በተዋበ ሰረገላ ቢረማመዱ ፣ በየጎዳናው ሁሉ እንደ ቅጠል እየተነጠፈ የሚሰግደው ቢበረክት ያለ ሰላም ምን ይኾናል? ያለ ሰላምስ ከንቱ አይደለምን? ያለ ሰላምስ ሁሉ አላፊ አይደለምን?
የጦር አበጋዙ ቢደረደር ፣ ቤተ መንግሥቱ ቢያምር ፣ ሁሉም ቢያሸበርቅና ቢደምቅ ያለ ሰላም አላፊ ጠፊ ነው። ጠዋት ታይቶ ማታ ይጠፋል ፤ አስጎምዥቶ ሳያጌጡበት ያልፋል ፤ ሳይቀምሱት አሳስቶ ይጠፋል። በምድር ሁሉ ያሉ ማጌጫዎች ፣ እጅግ የተወደዱ መዋቢያዎች ፣ በምድርም ያሉ መመኪያዎች ያለ ሰላም ባዶ ናቸው። ሁሉም ተደራርበው ሰላምን አይገዟትም፣ ሰላም ግን ሁሉንም ትገዛቸዋለች። አማርጠው የሚጠጡት ፣ አማርጠው የሚበሉት ፣ አማርጠው የሚለብሱት ፣ ለነገና ከነገ ወዲያ ለልጅ ልጅ የሚኾን ሀብት ቢያካብቱት ያለ ሰላም ከንቱ ነው። ሰላም ከሌለች ሁሉም እንደ ጥላ ያልፋሉ ፣ ሁሉም እንዳልነበር ይጠፋሉ።
ሰላም በጠፋች ጊዜ ጎዳናዎች ይዘጋሉ ፤ ውበትና መዋቢያዎች ይረግፋሉ ፤ የሚቦርቁ ልጆች ይቀጠፋሉ ፤ የሚመርቁ ሽማግሌዎች ያልፋሉ ፤ የሚያስተምሩ አባቶች ይጠፋሉ። አቅመ ደካሞች ያለ ጧሪ ቀባሪ ይቀራሉ ፤ እናቶች የማሕፀን ፍሬዎቻቸውን ተነጥቀው አብዝተው ያነባሉ ፤ አንጀታቸውን አስረው ያለቅሳሉ።
ሰላም የሁሉም መሠረት ናት። ሰላም የተገነባውን ታፀናለች ፤ የፈረሰውን ትገነባለች ፤ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ትሰጣለች ፤ የጨነቀውን ታረጋጋለች ፤ ያዘነውን ታፅናናለች። ደሴ ሰላም ውድ በኾነበት ዘመን ሰላምን ጠብቃለች፣ አስጠብቃለች። በቆየው እሴቷ ፣ አበውና እመው በያዙት ብልሃቷ ዛሬም ሰላሟን እንደጠበቀች በሰላምም እንደተጠበቀች ናት።
የደሴን ጎዳናዎች ተመላለስኩባቸው፣ ሰላማውያን የሚኖሩባቸው፣ ሰላማውያን የሚመላለሱባቸው ሰላማዊ ናቸው፣ የደሴን ነዋሪዎች ዘየርኳቸው፣ በሰላም የሚቀበሉ ደጋጎች ናቸው። ሁሉም የተዋበ ነው። ሁሉም የሚያስደንቅ ነው። በዚያ ያማረ ሰላም አለ።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሰላምና መከባበር ማስፈን ባለሙያ ብርሃኑ አራጌ የደሴ ከተማ ሕዝብ ሥልጡን ፣ ተግባቢነቱ ከፍ ያለ ፣ በሚነሱ ችግሮች ላይ የጋራ መግባባት ያለው መኾኑ ሰላምን እንዲጠብቅ አድርጎታል ይላሉ። ስለ ችግር ግልፅ የኾነ መረዳት ያለው እና ለመፍትሔው የሚሠራ ነው። ለግጭት የሚቸኩል የለም። ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ያቀርባል፣ በሥልጣኔም ይቀበላል ፣ ያለው የሥልጣኔ ዳራ በአንድነት እና በአብሮነት እንዲኖር አድርጎታል ነው ያሉት።
በደሴ ሰፊ ተግባቦት፣ ሰፊ አንድነት፣ የጠነከረ ሰውነት እና ኢትዮጵያዊነት አለ። የቀደመው የእሴት መሠረት ደሴን የተጠበቀች ከተማ አድርጓታል። የሰላም መጠበቁ ምክንያት ያለው መረዳት ፣ መግባባት እና አንድነት ነው። በደሴ ሰውነት ይቀድማል፣ ሰውነትም የተጠበቀ ሰላም እንዲኖር ማስቻሉንም ነግረውናል። የቆየው የእሴት ዳራ ለሰላሙ መጠበቅ አስተዋፅዖው ከፍ ያለ ነው።
ሁሉም ሰላሙን ይጠብቃል ሥራውንም ይሠራል ፤ ትኩረቱ ሥራ ላይ ነው ብለውናል። ሕግ አክባሪ እና በሕግና ሥርዓት ነዋሪ በመኾኑ ሰላም እንዲቀጥል አስችሏልም ነው ያሉን። የደሴ ሰው በውይይት እና በሠለጠነ መንገድ ችግሮቹን በመፍታት ያምናል ነው ያሉት ባለሙያው። የደሴ ሕዝብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ያቀርባል፣ መናገር የሚገባውን ይናገራልም ብለዋል።
ሌሎችም ከደሴ መግባባትን፣ ፍቅርን፣ እሴትን እና ሰላምን ሊወርሱ ይገባል ነው ያሉት። በግጭት ጥያቄን ከመፍታት በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አማራጮችን ማየት ይገባልም ብለዋል። በደሴ ከተማ ለሰላም ስጋት የሚኾኑ አዝማሚያዎች ሲኖሩ የደሴ ነዋሪዎች ይቆጣጠራሉ ፤ ከፀጥታ ኀይሎች ጋር በጋራ ይሠራሉም ነው ያሉን። ይሄም ሰላም ሁልጊዜ ፀንቶ እንዲኖር አድርጎታል።
የሰላም መምህርቷ፣ የፍቅር እመቤት ሁልጊዜም ሰላም አይለይሽ ፣ ሁልጊዜም ሰላም አይጥፋብሽ ፣ ሕዝብሽ ሁልጊዜ በሰላም ይኑሩብሽ ፣ ደስታና ፍቅር ይጽናብሽ። የመወደድ ግርማ አይጥፋብሽ።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!