“በአማራ ክልል 497 ትምህርት ቤቶች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል” የአማራ ክልም ትምህርት ቢሮ

43

ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ተከታታይ ሁለት ዓመታት እንደ ሀገር የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አስገዳጅ እንደኾነ አመላከች ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

በትምህር ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን አርሞ ለማስተካከል እንደ ሀገር የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀቶ ትግበራ ላይ ነው፡፡

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በሀገሪቱ የነበረው የሥርዓተ ትምህርት ፖሊሲ ትግበራ በተለይም በትምህርት ጥራት ላይ ውስንነት እንደነበረበት ሲነሳ ቆይቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የማስተካከያ እርምጃዎች ከተወሰደባቸው ሂደቶች መካከል ደግሞ የምዘና ሥርዓቱ አንዱ ነው፡፡ በአማራ ክልል በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመደበኛ፣ በማታ እና በግል የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመውሰድ 214 ሺህ 997 ተማሪዎች ምዝገባ አካሂደው ነበር ተብሏል፡፡

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን እንደ ክልል የውጤት ትንተና መግለጫ የሰጡት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኅላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ለፈተና ከተመዘገቡት መካከል 210 ሺህ 323 ተፈታኞች ፈተናውን ወስደዋል ብለዋል፡፡ ከተመዘገቡት መካከል ፈተናውን የወሰዱት 97 ነጥብ 8 በመቶ ናቸው ተብሏል፡፡

በክልሉ 574 ትምህርት ቤቶች የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስፈትነዋል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ 497 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ቢያንስ አንድ ተማሪ 50 በመቶ እና በላይ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል ብለዋል፡፡

77 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ እንኳን 50 በመቶ እና በላይ አላመጡም ተብሏል፡፡ እንደ ሀገር ከተመዘገበው አንጻር ሲታይ ክልሉ የተሻለ ቢኾንም ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በተፈጥሮ ሳይንስ 600 እና በላይ፤ በማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ 500 እና በላይ ከፍተኛ ውጤት ተብሎ ይያዛል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በክልሉ 60 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

በተፈጥሮ ሳይንስ 600 እና በላይ 43 ወንዶች እና 11 ሴቶች በድምሩ 54 ተማሪዎች አስመዝግበዋል፡፡ በማኅበራዊ ሳይንስ 500 እና በላይ 5 ወንድ እና 1 ሴት በድምሩ 6 ተፈታኞች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕክምና ተቋማትን ደኅንነት ማስጠበቅ ይገባል” የባሕርዳር ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
Next articleበኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛ ለማስቀረት የተደረገውን ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ።