
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጸጥታ ችግር አገልግሎቱ ተስተጓጉሎ የነበረው በባሕርዳር ከተማ የሚገኘው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ መደበኛ ሥራው ተመልሷል።
ባለፉት ቀናት በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ሕክምና ለማግኘት ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር የሆስፒታሉ የታካሚ ቤተሰቦች ለአሚኮ ተናግረዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ በባሕርዳር ጥበበ ግዮን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መጥተው ሲገለገሉ ያገኘናቸው የታካሚ ቤተሰቦች እንዳሉት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ በሕክምና ሂደቱ ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል።
የጤና ባለሙያዎች የሕክምና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለታካሚዎች በገንዘብ ጭምር በመደገፍ ተገልጋዮች ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም መሻሻሎች መኖራቸውን ያነሱት ተገልጋዮች በችግር ጊዜ የመጀመሪያ ተጋላጮች ሕሙማን በመኾናቸው ሁሉም ሰው ለሰላም መሥራት ይገባዋል ብለዋል።
የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘበናይ ቢተው፤ በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መስተጓጎል አጋጥሞት ነበር።
በተለይም ደግሞ በትራንስፖርት ፣በሠራተኞች ደኅንነት እና በግብዓት አቅርቦቱ ላይ ችግር በማጋጠሙ የተሟላ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም ነበር።
አሁን ላይ የተገልጋዮች ቁጥር መቀነስ እንዳሳየም ነው የነገሩን፡፡ ዳይሬክተሩ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ቦታቸው እንዲመለሱ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት ቀናትም የተሟላ ሥራ ይጀምራል ነው ያሉት። ሕሙማን የተሟላ ሕክምና እንዲያገኙ ሰላም ዋነኛው ጉዳይ በመኾኑ የሕክምና ተቋማትና ሠራተኞች ደኅንነት ሊጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!