
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሐምሌ 19/2015 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተሰጥቷል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና የተመዘገበው ውጤት ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ግድ የሚል መኾኑን አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ላለፉት ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ከመማር ማስተማር እስከ ትምህርት ፖሊሲ ፤ ከትምህርት ግብዓት እስከ ምዘና ሥርዓት ለውጥ ያስፈልገዋል የሚሉት በርካቶች ነበሩ፡፡ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በተለየ መልኩ የተሰጠው ብሔራዊ ፈተና የችግሩን መጠን እና ግዝፈት አጉልቶ አመላክቷል ተብሏል፡፡
በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንደ ሀገር 50 በመቶ እና በላይ ያስመዘገቡ ተፈታኞች 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኅላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የውጤት ትንተናን አስመልክቶ በቢሯቸው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም 210 ሺህ 323 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በክልሉ በሚገኙ 10 የከፍተኛ ትምህርት ተቋምት እና በ25 የፈተና ማዕከላት ፈተናቸውን ወስደዋል ብለዋል፡፡ ዶክተር ሙሉነሽ “8 ሺህ 434 ተማሪዎች 50 በመቶ እና በላይ ውጤት አስመዝግበዋል” ነው ያሉት፡፡ 50 በመቶ እና በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 0 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ ተመዝግቦበታል ተብሏል፡፡
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ክልሉ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ኾኖ የተመዘገበ ነው ያሉት ኅላፊዋ ችግሮችን ፈትተን እና ተማሪዎች የተሻለ ተዘጋጅተው ቢፈተኑ አበረታች የሚባል ውጤት ሊገኝበት የሚችል እንደኾነ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ያለው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ትንተና እንደሚያመላክተው የተመዘገበው አማካይ ውጤት 30 ነጥብ 11 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በኬሚስትሪ የትምህርት ዓይነት ሲኾን 33 ነጥብ 42 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ በክልሉ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበበት የትምህርት ዓይነት ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ መስክ የሚሰጠው የሒሳብ ትምህርት ሲኾን 26 ነጥብ 75 በመቶ ስለመኾኑ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!