
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምርት ማምረት የጀመሩ እና በማሽን ተከላ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን፣ የሸድ ግንባታ፣ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠውን ዘመናዊ መናኻሪያ እና ሌሎችም የልማት እንቅስቃሴዎች በክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ተጎብኝተዋል።
የሥራ ኀላፊዎቹ በማኅበራዊ ተቋማት ማስፋፊያ ዘርፍም የትምህርት ቤት ግንባታ እና የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አገልግሎት አስጣጥን ተመልክተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ኮምቦልቻ ከተማ ለተለያዩ ኮሪደሮች መውጫ በር በመኾኗ ለኢንዱስትሪ ከተማነት ተመራጭ ናት ብለዋል። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የምርት አቅርቦት ተደራሽ እንዲያደርጉ እንሠራለን ብለዋል።
ከተሞችን በማስተር ፕላን እንዲመሩ፣ ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን የተማረ የሰው ኃይል በማፍራትና በዘርፉ የሚገጥማቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ቀርቦ በመፍታት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚገባም ዶክተር አሕመዲን ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት እንዲያመርቱ እና ምርታቸውን ወደተፈላጊው ቦታ ለማድረስ “ሰላም ” ወሳኝ በመኾኑ ለዘላቂ ሰላም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ በ2015 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት። በፌደራል መንግሥትም በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን አብራርተዋል።
ከኮምቦልቻ ከተማ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የግሉ ዘርፍ የሚገጥማቸውን ችግሮች በመፍታት በቂ ምርት እንዲያመርቱ በደረጃው ያለው መዋቅር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!