“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረጉት ምክክር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት ያሳየ ነው” ቢልለኔ ስዩም

41

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ያደረጉት ምክክር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት ያሳየችበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በቻይና እያደረጉ የሚገኙትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋዊ አቀባበል ማድረጋቸውንና የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት በሚያመላክት መልኩ መከናወኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ መሆኑን መግለጻቸውንና አኹንም የበለጠ ከፍ ለማድረግ ፍላጎት መኖሩን መጥቀሳቸውን አመላክተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር ግንኙነት ማጠናከሪያ መንገዶችን ማንሳታቸውንም ገልጸዋል።

ከውይይቱ በኋላም ሁለቱ መሪዎች በተገኙበት በሀገራቱ መካከል አስራ አራት የሚሆኑ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶች መፈረማቸውንም አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለሀገር በመሥራት ሊኾን እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleምክር ቤቱ 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።