
ጎንደር: ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ በመንግሥት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ወገኖች ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል። አስተያየት ሰጭዎቹ መንግሥት በማኅረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ ይገባዋልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ኅላፊ መላከ ስብሀት አባ ገብረሥላሴ ላቀው ወደ ሰላም መንገድ መምጣት ለሀገርም ለሕዝብም የሚበጅ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል። ሰላምን ለማጽናት መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኤርሚያስ ቢራራ የሚነሱ ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል። በመንግሥት በኩል የቀረበውን የሰላም አማራጭ መጠቀም ተገቢ መኾኑንም አሳስበዋል።
ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ አስፈላጊነት ያነሱት አቶ ኤርሚያስ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገር ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
አቶ ኤርሚያስ ጦርነት የሚያስከትለውን ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ተፅእኖዎች በመገንዘብ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ቀዳሚ የመፍትሄ አማራጭ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!