የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም ለሰላም መሥራት ይገባዋል ተባለ።

26

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መዳረሻ መስህብ ቦታዎች ባለቤት ነው። የቱሪዝም ዘርፉ ካለው ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ ባለፈ ሠፊ የሥራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ አለው።

በተለይም ደግሞ ከመስከረም እስከ ጥር ጎብኝዎች ለመዝናናት፣ ለስብሰባ፣ ለንግድ፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ክልሉ የሚመጡበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት የሚታይበት እንደኾነ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ ነግረውናል።

ይሁን እንጅ ከ2011 ዓ.ም በኋላ በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች እንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል።

ዘርፉ በ2015 ዓ.ም በነበረው አንጻራዊ ሰላም በተለይም ደግሞ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር እድገት ቢያሳይም አሁን ላይ በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ዳግም ሳንካ አጋጥሞታል።

✍️. በ2011 ዓ.ም ከ11 ሚሊዮን 666 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ከ1 ቢሊዮን 552 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቶ ነበር።

2015 ዓ.ም ደግሞ ከ15 ሚሊዮን 113 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 5 ቢሊዮን 254 ሚሊዮን ብር ገደማ ተገኝቷል።

✍️. በ2011 ዓ.ም 207 ሺህ የነበረው የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በ2015 ዓ.ም ወደ 29 ሺህ አሽቆልቁሏል። የገቢ መጠኑም ከ955 ሚሊዮን ብር ወደ 98 ሚሊዮን ብር መውረዱን ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት።
በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ፡-

✍️. ከ21 ሚሊዮን 376 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 3 ቢሊዮን 228 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብር ለመሰብሰብ ሲታቀድ

✍️. ከ29 ሺህ 630 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ደግሞ 136 ሚሊዮን 358 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ በክልሉ የተከሰው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዚህም በዘርፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከኾኑ አስጎብኝዎች ባለፈ በዘርፉ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይም የምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ አስከትሏል። ዘርፉን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም ለሰላም መሥራት ይገባዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በሮም የዓለም ምግብ ፎረም ላይ ተሞክሮዎቿን ታቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል።
Next articleችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሕዝቡ ሚና የጎላ ነው ተባለ።