
ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሐሰተኛ ምስክር፣ የመረጃና ማስረጃ እጦት፣ ብልሹ አሠራር እና መሰል ጉዳዮች በክልሉ የሚሰጠውን የፍትሕ ሥርዓት ጥራት እና ተዓማኔነት ጥርጣሬ ውስጥ ጥለውት ቆይተዋል፡፡
በተለይም ባለፈው ዓመት በፍርድ ቤቶች ለታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጉድለት ምክንያቶች ለይቶ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ አሠራር ለመከተልም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንም ከዞን ፍርድ ቤቶች ጋር እየመከረ እንደሚገኝ ነው የተመላከተው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤቶችን አሠራር በማሻሻልና ተደራሽነታችውን በማስፋት ለፍትሕ ጥራትና ቅልጥፍና ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ እንደሚገኝም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
በባለፈው ዓመት ሐሰተኛ ምስክር፣ የመረጃ እጦት፣ ብልሹ አሠራርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳች የፍትሕ ሥርዓቱን ፈትነውት እንደነበርም ፕሬዘዳንቱ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዓመት ግን የፍርድ ቤቶችን አሠራር በማሻሻልና ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለፍርድ ጥራትና ቅልጥፍና ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራ ነው የነገሩን፡፡ ለዚህም ጥናት መካሄዱን ነው ያስገነዘቡት፡፡ በጥናቱም መሠረት ዘላቂ የኾነ ሥራ ተሠርቶ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የሥነ ምግባር ጉድለት በሚስተዋልባቸው ዳኞችና የአሥተዳደር ሠራተኞች ላይም የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በሐሰተኛ ምስክር ምክንያት የፍትሕ ሥርዓቱ የሚዛባበት ኹኔታ መስተዋሉን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ኅብረተሰቡ ይህን ችግር ራሱ ሊፈታ የሚችልባቸውን አሠራሮች ለመከተልም መታሰቡን ነው ያብራሩት፡፡
የፍርድ ሂደቱን በማገዝ በኩል የተዘዋዋሪ ችሎት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ አሠራሩ ቀልጣፋ እንዲኾን ትኩረት ተሠጥቶ መሠራት ስላለበት ለዚሁ ተግባር ርብርብ እንደሚደረግም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!