
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሉዓላዊነትና የነፃነታችን ዓርማ የኾነውን ሰንደቅ ዓላማችንን የሕይወት መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሸነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ገልጸዋል።
16ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በፌዴራል ፖሊስ ቅጥር ግቢ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ጊዜ፤ አባቶቻችን ያስረከቡንን የሉዓላዊነት ምልክት፣ የነፃነታችን ዓርማ እና የክብራችን መገለጫ የኾነውን ሰንደቅ ዓላማችንን የሕይወት መስዕዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን ብለዋል።
በመላው ሀገሪቱ ያሉ የፖሊስ አባላት ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ዘወትር ዘብ መሆኾናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
በዓሉ በፓናል ውይይትና ሌሎች የሰንደቅ ዓላማን ክብር ከፍ በሚያደርጉ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው መኾኑን ኢዜአ ዘግቧል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 ተደንግጎ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!