“ባለፉት ሦስት ወራት ከ5 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ ተሰብስቧል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ

30

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት ከ71 ቢሊዮን 650 ሚሊየን በላይ ብር ገቢ በመሰብሰብ የኅብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ባለፉት ሦስት ወራት ቢሮው 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ግብር ለክልሉ ነዋሪዎች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መልስ ለመሥጠት አስፈላጊ መኾኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ገቢ ከሌለ ልማት፣ ገቢ ከሌለ እድገት ብሎ ነገር እንደማይታሰብም አንስተዋል፡፡

ክልሉ በሩብ ዓመቱ 17 ቢሊዮን 912 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ቢያቅድም በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት እቅዱን ማሳካት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 33 በመቶ ብቻ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ብር መቀነሱንም ጠቁመዋል፡፡

ሰላም ለገቢ ሥራ እስትንፋስ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ሰላም ባለመኖሩ የሚፈለገውን ገቢ መሰብሰብ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት እቅዱን ማሳካት ባይቻልም በተቻለ መጠን በችግር ውስጥም ኾኖ ገቢው እንደተሰበሰበ ነው የተናገሩት፡፡

በየደረጃው ያለው የገቢ ሰብሳቢ ተቋም የገቢ ሥራ የሕልውና ሥራ መኾኑን ተገንዝቦ ከሕዝቡና ከግብር ከፋዮች ጋር በመሥራቱ የመጣ ነውም ብለዋል፡፡

ቁርጠኛ ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች በመኖራቸው ግብር የኅልውና ጉዳይ ነው ብሎ ሕዝብን የማግባባቱ ሥራ በሰፊው መሠራቱንም ጠቁመዋል።

ተቋሙ የሕዝብ ተቋም ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ሕዝቡም ይህን ተረድቶ ግብሩን በወቅቱ ለመክፈል እንዲዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር ፣ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ ባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብር በሰፊው የተሰበሰበባቸው አካባቢዎች መኾናቸውንም አቶ ታዘባቸው አንስተዋል፡፡

የግብር ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው የሚለውን ገዥ ሃሳብ ለሕዝቡ ግልጽ መደረጉ ለሥራው ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ሥራውን አጠናክሮ ለመሥራት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡

ወደ ሥራ ያልገቡ አካባቢዎችም ሥራው የኅልውና ጉዳይ መኾኑን ተገንዝበው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግም መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ ፦ ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር በሚያጠናክሩባቸው መንገዶች ዙርያ ተወያዩ።
Next article“የሉዓላዊነትና የነፃነታችን ዓርማ የኾነውን ሰንደቅ ዓላማችንን የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንጠብቀዋለን” ኮሚሸነር ደመላሽ ገብረሚካኤል