
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር በሚያጠናክሩባቸው መንገዶች ዙርያ ተወያይተዋል።
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት በሚያመለክት መልኩ ተከብሯል።
በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅትም መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ሃብት ትብብር ግንኙነት ማጠናከሪያ መንገዶች ላይ መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ሁለቱ ሀገራት በማደግ እና በመጎምራት ላይ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤቶች እንደመሆናቸው በጋራ የማደጊያ መንገዶችን ሊቀይሱ እንደሚችሉ አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በበኩላቸው የመንግሥታቸውን ባለብዙ ዘርፍ የእድገት አላማ ብሎም የተገኙ ድሎችን አካፍለዋል።
በተጨማሪም ከቻይና ጋር የንግድ ግንኙነቶችን የማስፋፋትን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው አንስተዋል።
ከሁለትዮሹ ውይይት በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ሊ ኪያንግ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ መስኮች አስራ ሁለት ያህል የትብብር ስምምነቶች ብሎም ሁለት የፍላጎት ሰነዶች በተፈረሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!