
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ በመኾኑ ዘወትር ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ የኾነውን ሰንደቅ ዓላማ ዘወትር ልንጠብቀውና ልናከብረው ይገባል ብለዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማችን ብሔራዊ መለያችን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ ሁሌም የሚገባውን ክብር ልንሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።
ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ብዙዎች መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰው፣ ክብሩን እና የበላይነቱን ሁሌም ማሳየት ይገባል ነው ያሉት።
ኢዜአ እንደዘገበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን፣ የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችን እና የኢትዮጵያዊነታችን አርማ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!