
ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተፈጠረው ወቅታዊ የሰላም እጦት ምክንያት ለመበተን ተዳርገናል ሲሉ የጉና አትሌቲክስ ክለብ አትሌቶች ገልጸዋል። በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የሰላም እጦት እያሳያቸው ያሉ ምልክቶች ሰላም ከሌለ ምንም እንደማይኖር ነው።
በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ ውስጥ በአማራ ዉኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን (አዉሥኮ) አትሌቲክስ ክለብ ስር የሚሠለጥኑ አትሌቶችንም ይሄው የሠላም እጦት ችግር ከዓላማችን አደናቅፎናል ይላሉ።
አትሌት ጀንበሩ ሲሳይ እና ይኸይስ አበባው ሀገርን ወክለው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመኾን ህልም ይዘው በአዉሥኮ አትሌቲክስ ክለብ ታቅፈው በጉና ተራራ ላይ እየሠለጠኑ ነበር። ይሁንና የሰላም ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል።
የሰላም እጦቱን ተከትሎ የተፈጠረው ምጣኔ ሃብታዊ ምስቅልቅልም ሥልጠናቸውን በተሳካ ኹኔታ እንዳያካሂዱ አድርጓል።
አትሌት ጀንበሩ በሰላም እጦት ምክንያት ልምምድ ቀንሰናል ብሏል። ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ አትሌቶችም ለመመለስ በመቸገራቸው በሥልጠና ማዕከሉ 10 ሠልጣኞች ብቻ ቀርተናል ነው ያለው።
የማሰልጠኛ ማዕከሉ ተስማሚ ቢኾንም በሰላም እጦት ችግር ለመበተን ተዳርገናል ብሏል። በሀገር አቀፍም ኾነ በክልል ደረጃ ለመወዳደር የሰላም እጦት የፈጠረው ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸው ነው አትሌት ይኸይስ የገለጸው።
በአዉሥኮ የጉና አትሌቲክስ ክለብ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጥላሁን አማረ በጸጥታ ችግር ምክንያት ክለቡን በቅርበት ለመምራት እንዳስቸገረ ገልጸዋል። በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያትም ውላቸውን በጨረሱ አትሌቶች አዳዲሶችን ለመተካት፣ በዕቅድ ለመምራት፣ በአካል ተገኝቶ ለማወያየትና ለመሥራት አለመቻሉን ነው የተናገሩት።
ኮርፖሬሽኑ አትሌቶቹን ሊያግዝ የሚችለው ሠርቶ ትርፍ ሲያገኝ ብቻ ነው ብለዋል አቶ ጥላሁን። በየአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ሠርቶ ማትረፍ ካልቻለ ችግሩ የደመወዝ ማነስ ብቻ ሳይኾን ማሰልጠኛ ማዕከሉ ተዘግቶ አትሌቶቹም ሊበተኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አትሌቶች የክልሉን ብሎም የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ኾነው እንዲኮተኮቱ እየተሠራ እንደነበርም አንስተዋል። የሰላም ችግር የበርካታ መልካም ጅማሮዎች መሰናክል መኾኑን በውል በመረዳት ሁሉም ለሰላሙ ዘብ መቆም እንደሚገባውም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። በክልሉ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ የተጀመሩ መልካም ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ እና ዘርፈ ብዙ ልማት ለማካሄድ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!