“በሰንደቅ ዓላማችን ሥር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እናፀናለን!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

30

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ16ኛ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።
ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ የነፃነታችን አርማና የክብራችን መገለጫ ነው፡፡ ሰነደቅዓላማችን ከትውልድ ትውልድ የተሸጋገረ፣ የጀግኖች አባቶቻችን የደማቸው ፍሳሽ፤ የአጥንታቸው ክስካሽ እንዲሁም የመስዋዕትነት ውጤት የሆነ የድል ሰንደቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፣ የሕዝቦችን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ጀግኖች ኢትዮጵያዊን ለሰንደቅ ዓላማችን ፍቅርና ክብር በአንድነት መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነታችን የተከፈለ መስዋዕትነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የሀገራችን ሉዓላዊነት ምልክት የኾነው የሰንደቅ ዓላማችን ፀንቶ የቀጠለው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በከፈሉት መስዋእትነት ነው፡፡

ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ 16ኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ሉዓላዊነታችን እና የኅልውናችን ዋስትና መኾናቸውን ታሳቢ ልናደርግ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ኅብረ ብሔራዊ ሀገር ናት፡፡ እጅግ ብዙ ባሕሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ መልከአ ምድርና የአየር ጠባዮች፣ ፍላጎቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምቅ ሀብቶች ያላት ብዝኃነት መገለጫዋ የኾነች ዕፁብ ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያችን ብዙ ኾና አንድ፤ አንድ ኾና ደግሞ ብዙ ነች፡፡

በዛሬው ዕለት የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከበር እነዚህን ኹለት የሀገራችንን ምሶሶ የኾኑ መገለጫዎች መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትም በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ ክብር ከፍ ይላል፡፡ የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ በዘላቂነት የሚቀጥለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር በሚከናወነው ጠንካራ ሥራ መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከትላንት እስከ ዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት በደማቸው ጠብቆ አቆይቷል፣ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርጓል፡፡ የዛሬ ትውልድ በአባቶቹ የሕይወት መስዋእትነት ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ሀገር በላቡ ማፅናት ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ ላይ ሉዓላዊነታችን በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሀገራችንን ከልመና ነፃ ስናወጣት ነው፡፡

ይህ የሚረጋገጠው ትውልዱ ያለበትን እዳ ተገንዝበው በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ በላቡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሲያረጋግጥ ነው፡፡ የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ሲኾን የማንነታችን መገለጫ፣ ሰንደቅ ዓላማችንም ልዕልናው ይጨምራል፡፡ መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ያለንን ክብርና ፍቅር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ሊያስጠብቁ በሚችሉ ክንውኖች ላይ በመሳተፍ በተግባር ማሳየት ይገባናል፡፡ የሀገራቸውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መስዋዕትነት የሚከፍሉትን አካላት እንደ ወትሮው ኹሉ በማክበር ለሰንደቅ ዓላማችን ዘብ መቆማችንን በተጨባጭ ማስመስከር ይጠበቅብናል፡፡

ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንንና ሉዓላዊነታችንን አፅንተን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በከፍታ እናውለበልባለን!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ኢኳቶርያል ጊኒን 4 ለ1 አሸነፈች።
Next articleበሰላም እጦት ምክንያት ለመበተን ተዳርገናል ሲሉ የጉና አትሌቲክስ ክለብ አትሌቶች ገለጹ።