
ሁመራ: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ በኮማንድ ፖስት ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ 284 ግለሰቦች በብዓከር ማሠልጠኛ ተቋም የተሃድሶ ሥልጠና አጠናቅቀው ተመርቀዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ብርጋዴል ጀኔራል ወርቅነህ ጉዴታ የ503ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ፤ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ የ503ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ፤ ኮሎኔል ኪሮስ ጎይቶም 503ኛ ክፍለ ጦር የሥነ ልቦና ግንባታ ኀላፊ ተገኝተዋል።
ጦርነት የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ ፤ የሰው ሕይወት የሚያጠፋ ፤ አካል የሚያጎድልና ንብረት የሚያወድም በመኾኑ ከጦርነት ይልቅ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ የ503ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ወርቅነህ ጉዴታ አመላክተዋል።
ሰላም የሀገርን ኢኮኖሚ የምንገነባበት በመኾኑ ከሥልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀት በመጠቀም የአካባቢያችሁን ኅብረተሰብ ስለ ሰላም በማስተማር የሰላም አርዓያ ልትኾኑ ይገባል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች መሥዋዕትነት እየከፈለ የሚኖር መኾኑን ያነሱት ብርጋዴል ጀኔራል ወርቅነህ ጉዴታ ወቅቱ አዝመራ የሚሰበሰብበት ፤ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ የሚያቀኑበት በመኾኑ ወደ ልማትና ሰላም ልትሰማሩ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የብዓከር ተሃድሶ ማሠልጠኛ ተቋም አሥተባባሪ አቶ ሳሙኤል ሲሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ፤ በደቡብ ጎንደር ፤ በሰሜን ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር ለነበሩ 284 ግለሰቦችን ከመስከረም 25 እስከ ጥቅምት 4/2016 ዓ.ም የተሃድሶ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
ሥልጠናው በዋናነት በሰላም አስፈላጊነት ፤ በግጭት አፈታትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በቂ ግንዛቤን የጨበጡበት ነው ብለዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ሠልጣኞች በሰላምና በውይይት ችግሮችን መቅረፍ እንደሚችሉ የተረዱበት እንደኾነም አንስተዋል።
በበዓከር የተሃድሶ ማሠልጠኛ ተቋም ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው በመመረቅ ላይ ያገኘናቸው የሥልጠናው ተሳታፊዎች ጦርነት የሀገርን አንድነት የሚያጠፋና ለውድመትና ለእልቂት የሚዳርግ በመኾኑ ችግሮችን በአፈሙዝ ሳይኾን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ተቀዳሚ ምርጫ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
በተሰጣቸው ሥልጠና መሠረት የሰላም አርዓያ ለመኾን እንደሚተጉ ያነሱት ሠልጣኞቹ መንግሥት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በማድመጥ ሊመልስ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት አሁን ላይ በሩን ለሰላም ክፍት ማድረግ እንደሚገባው የገለጹት ሠልጣኞቹ የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ ፣ የአማራ ሕዝብ በክልሎች ተዘዋውሮ የመሥራት መብት እንዲከበር ፤ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾንና ሌሎች የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!