
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አፋር እና አማራ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ሁለት ክልሎች እና ጎረቤታሞች ብቻ ሳይኾኑ ለዘመናት ታሪክ፣ ድንበር እና ኢትዮጵያዊ ፍቅርን የሚጋሩ ክልሎች ናቸው፡፡ “እንኳን ሰዎቹ ግመሎቻቸው እንኳን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በርቀት ያውቃሉ” የሚባልላቸው አፋሮች ከወንድም እና እህት አማራ ሕዝብ ጋር ያላቸው ሥነ-ልቦናዊ ቁርኝት ዘመናትን ያስቆጠረ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከከፍተኛው የራስ ዳሽን ተራራ እስከ ዝቅተኛው የዳሎል መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሁሉን በየፈርጁ አስማምታ ያቀፈችው ኢትዮጵያ የሕዝቦቿም ስብጥር ያንኑ ያክል በልዩነት የደመቀ ውበት እንዳለው ይነገራል፡፡ የተለያየ ቋንቋ መናገር በተለያየ መልካዓ ምድር ላይ መስፈር፤ የተለያየ ሃይማኖት መከተል የባሕል ልዩነት መኖር የትናንቷን ኢትዮጵያ እንዳላደበዘዛት ሁሉ የነገዋንም ኢትዮጵያ አያሰጋትም ይላሉ፡፡
ከቀናት በፊት ብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መሪዎቹን በተለያዩ ከተሞች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ በባሕር ዳር ተመድበው ሥልጠናውን የሚወስዱ ሠልጣኝ መሪዎችም ባሕር ዳርን ተላምደናታል ወደናታልም ይላሉ፡፡ ባሕር ዳርን ከዚህ ቀደም እንደሚያውቋት የነገሩን እና ከአፋር ክልል የመጡት ሠልጣኝ ፋጡማ ሙሳ “የመጣሁት ወደ ሁለተኛዋ ቤቴ ነው” ብለውናል፡፡
በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር አሁን ካለበት ነባራዊ ኹኔታ ጋር በማይገናኝ መንገድ ሲገለጽ ነበር ያሉት ፋጡማ ሙሳ በባሕር ዳር ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለብዙዎች ግርምትን ፈጥሯል ብለዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ ችግር ይኖራል ነገር ግን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንጂ ቱሪዝሙንም ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴውንም በሚጎዳ መንገድ ወደ ግጭት መግባት የሚያስከፍለው ዋጋ አውዳሚ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ እና አፋር ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስራቸው ድንበር ከመጋራት አልፎ ሥነ-ልቦናዊ ትስስር ያለው ነው ያሉት ሠልጣኟ ይኽንን ወንድማማችነት እና እህትማማችነት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡ ኅብረ ብሔራዊቷ ኢትዮጵያ እንደ ኅብረ ቀለማት የደመቀ ማንነት አላት ያንን የደመቀ ማንነት ለማስቀጠል መነጋገር እና መደማመጥ ይጠይቀናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያዊነት በልዩነት እና ኅብረ ብሔራዊነት መካከል የሚጸና ድልድይ በመኾኑ አንዱ ሌላውን በሚገባ ለመረዳት እና ለማወቅ ጊዜ መውሰድ እና መትጋት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ የመሪዎች ሥልጠና ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ከመጡ ወንድም ሕዝቦች ጋር የተዋወቅንበት በመኾኑ ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ እውን መኾን መነሻ ኾኖ ያገለግላልም ነው ያሉት፡፡
ባሕር ዳር ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅማ ገጽታዋን ከመላው ኢትዮጵያ ለመጡ ሠልጣኞች መሸጥ አለባት ፤ በቆይታዬ ያስተዋልኳቸው ነገሮች ግን መልካም ናቸው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!