
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቆላ ከደጋ፤ ክረምት ከበጋ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ገጽታ እና እውነታ ያላት ጥንታዊትም ታሪካዊትም ሀገር ናት፡፡ ምንም እንኳን ስለኢትዮጵያ የውጭዎቹ አሳሾች አንጥረው እና አብጠርጥረው ቢያውቋትም የሚጽፉላትም ኾነ የሚነግሩላት የሚጠቅማትን ሳይኾን የሚጠቀሙበትን ለይተው ነው፡፡
የውጭ ጎብኝዎች እና የታሪክ መርማሪዎች የጻፉላቸውን የተሳሳተ ትርክት ብቻ እንደድርሳን እየደገሙ እና እየደጋገሙ አንዱ ሌላውን በአግባቡ ሳይረዳው ዘመናት አልፈዋል፡፡ በተለይም ባለፉት ቅርብ ዓመታት ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ ከሀገር በታች የኾነ ማንነት የመታገያም፤ የመታያም መስመር መኾኑ ሀገራዊ አንድነት ችላ እንዲባል አድርጓል ሲሉ የሚወቅሱ በርካቶች ናቸው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ ላይ ለሚገኙ መሪዎቹ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ በባሕር ዳር እየተሰጠ ባለው ድርጅታዊ ሥልጠና ላይ ያገኘናቸው መሪዎችም ከተማዋ ፍጹም ሰላማዊ እና ሕዝቡም እንግዳ ተቀባይ ኾኖ እንዳገኙት ነግረውናል፡፡
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ልዩነት የሌለው ወንድም ሕዝብ እንደኾነ እናውቃለን ያሉን ከደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ የመጡት ሠልጣኝ አቶ ጣሰው ከበደ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ኢትዮጵያዊነትም ዛሬ የተፈጠሩ ማንነቶች አይደሉም የሚሉት አስተያየት ሰጭው፤ ምናልባትም የምናስቀጥላት እንጂ የምንፈጥራት ሀገር የለችንም ነው ያሉት፡፡ ልዩነት አብዝቶ የሚቀነቀነው አዲስ ለሚፈጠር እንጂ ለነበረ እና ለሚኖር ማንነት አይደለም ብለዋል፡፡
“እኛ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን በወጉ የተረዳናት አይመስለኝም” ያሉን አስተያየት ሰጭው ኢትዮጵያም ኢትዮጵያዊነትም ከስጋ እና ከአጥንት ፤ ከደምና ላበት የጸናች ሀገር በመኾኗ ከሚነጣጥሏት ይልቅ አንድ የሚያደርጓት ይበዛሉ ብለውናል፡፡ የትናንቷ ኢትዮጵያ ያለድካም አልተሠራችም፤ እልፎች ስለሀገር በርካታ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ በዚህ ትውልድ መዳፍ ውስጥ ያረፈችው ኢትዮጵያም በውጣ ውረድ ውስጥም ቢኾን ትጸናለች ብለውናል፡፡
ወደ አማራ ክልል ከመምጣታቸው በፊት በክልሉ የተረጋጋ ሕዝብ እና ሀገረ-መንግሥት ያለ አይመስልም ነበር ያሉት አቶ ጣሰው ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ ያስተዋሉት ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳስገረማቸውም ነግረውናል፡፡ የከተማዋ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ እና ከተማዋም ውብ መኾኗን ገልጸው በፖለቲካ አመራሩ የተጀመረው ኅብረ ብሔራዊ ጉዞ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችም መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
ባለንበት ዘመን ሰው የሚረዳህ ራስህን ለሰው ባስተዋወቅክበት እና በገለጥክበት ልክ ነው ያሉት አቶ ጣሰው ክልሉ ይኽንን የመሰለ ማራኪ መልካ ምድር፣ የጣና ሐይቅን የሚያክል ተፈጥሯዊ ጸጋ እና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ይዞ የተነገረለት እጅግ በተሳሳተ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
ሕዝቡ እና የፖለቲካ መሪዎች የአካባቢውን ትክክለኛ ማንነት እና ምንነት በአግባቡ ማስረዳት ይኖርበታልም ብለውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!