
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ በመላው ሀገሪቱ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ድርጅታዊ ሥልጠና እየሰጠ ነው። ሰልጣኞቹ ከመላው የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በመኾናቸው ኅብረ ብሔራዊነት ኢትዮጵያን የማጽናት ሌላኛው ተምሳሌት ነው ይላሉ።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደመጡ የነገሩን ወይዘሮ አበሻ ባይነት ስለአማራ ክልል ሰላም የሚወራው እና በቆይታየ በባሕር ዳር ከተማ ያየሁት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተለያዩ ናቸው ብለዋል። ክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይታወቃል፤ ነገር ግን ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት በመኾኑ በከተሞች የሚስተዋለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ፍጹም የተረጋጋ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቱባ ባሕል፣ ውብ የተፈጥሮ ጸጋ እና ሕብረ ብሔራዊ ማንነት የተንሰላሰለባት ከተማ ናት። “ባሕላዊ፣ መልካ ምድራዊ እና የእምነት ልዩነቶቻችንን ኅብረ ብሔራዊ ጌጦቻችን አድርገን ለሀገራዊ አንድነት ተቀራርበን መሥራት ይጠበቅብናል” ነው ያሉት።
ከሀረር እንደመጡ የነገሩን ሌላው ሰልጣኝ ብራቱ ተፈሪ ባሕር ዳርን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳዩት ነግረውናል። የከተማዋ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነት፣ ትህትና እና ፍቅር በሩቅ ከሚወራው ይለያል ነው ያሉት። በከተማዋ በቆዩባቸው ቀናት ከሕዝቡ የተመለከቱት አሰተዋይነት እና ቅንነት በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ የሚያደርጋቸው እሴት እንደኾነም ነው ያስረዱት።
“ወደ ባሕር ዳር መምጣቴ ኅብረ ብሔራዊቷን ኢትዮጵያ ለመመልከት እና ለመረዳት እረድቶኛል” ያሉት ሰልጣኙ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ወደ ባሕር ዳር ከመምጣታቸው በፊት ስለክልሉ የሚወራው ካለው ነባራዊ ሁኔታ እጅግ የተጋነነ ነውም ብለዋል። የጸጥታ ችግር ያለው አማራ ክልል ብቻ ባለመኾኑ የተለየ ሃሳብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በበሰለ፣ በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን በውይይት መፍታት መልመድ ይገባል ብለዋል።
ሰልጣኞቹ በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!