“ከሁሉም ኢትዮጵያዊነት ይቀድማል” የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች

29

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ “ከእዳ ወደ መንዳ” በሚል መሪ ሐሳብ ለመሪዎቹ ስልጠና እየሠጠ ነው፡፡ በባሕርዳር እየሰለጠኑ የሚገኙት የፓርቲው መሪዎች በባሕርዳር የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡

ስልጠናው የመሪዎችን አቅም በማጎልበት፣ የጋራ ሀሳብ በማመንጨት እና የጋራ ሀገርን መገንባት ለማስቻል ያለመ እንደኾነ ሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው የተገኙ መሪዎች ሀገራዊ አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት ቱባ ማማ በአንድ ፓርቲ ሥር ያሉ፣ በሀገሪቱ ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ መሪዎች በአንድነት ስልጠና መውሰዳቸው ለአንድነት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል፡፡በጋራ በመወያየት ያሉብን ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችሉናልም ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ሰልጣኙ በአንድነት መወያየት እና በአንድነት መሥራት ሰላምን ያሰፍናል ነው ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ተነጋገሮ መፍታት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው በርካታ ሃሳቦች እየተነሱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ብሔር ሳይኾን ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚለው መንፈስ እንዲጎለብት ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

ከአፋር ክልል የመጡት ነስራ ዑዳ የጋራ ሀሳቦችን ማንሳት እና በጋራ ሀሳቦች ላይ መሥራት አንዲት ኢትዮጵያን ለማጽናት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማሳደግ እና ለማልማት አንድነት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ በመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ መሪዎች መገናኘት በየአካባቢው ያለውን ሃሳብ እና ተሞክሮ ለማወቅ እንደረዳቸውም ተናግረዋል፡፡

ብሔርና ብሔርተኝነት የሀገር ፍቅርን እንደሚጎዳና አንድነትን እንደሚያቀጭጭም ገልጸዋል፡፡ ብሔርን መሠረት አድርገው የሚነሱ ችግሮች የሰላምና የጸጥታ ችግር ምክንያት መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ከሁሉም ነገር ኢትዮጵያዊነት ይቀድማልም ብለዋል፡፡ አንደኛው ክልል ሰላም ሳይኾን ቀርቶ ሌላኛው ክልል ሰላም የሚኾንበት ምክንያት እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ ሀገር ሰላም የምትኾነው ሁሉም በአንድነት ሲሠራና በሁሉም አካባቢ ሰላም ሲኾን መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልሎች እኩል ልማትና ተጠቃሚነት በድምሩ ሀገርን እንደሚያሳድግም ገልጸዋል፡፡ ብሔርን ለበጎ ነገር እንጠቀምበት ያሉት ሰልጣኙ ብሔርን ተገን አድርጎ የሚፈጸሙ ያልተገቡ ሥራዎች የሀገርን አንድነት እንደሚያናጉም አመላክተዋል፡፡ ብሔርን ለጸብ መነሻ ሳይኾን ለአንድነት ማጎልበቻ ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል፡፡

ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በቁርጠኝነት መመለስ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የአመራር ክፍተት ሲፈጠር ችግሮች እንደሚፈጠሩም ገልጸዋል፡፡ ለመረጠ ሕዝብ የሚገባውን ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ የጋራ ውይይታቸው የሕዝብን ጥያቄዎች ለመፍታት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል፡፡

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡት ባርክደርድም አሕመድ ከተለያዩ አካባቢዎች ተገናኝቶ በጋራ በመወያየት የነበሩትን ብዥታዎችና መጠራጠሮችን ቀርፈናል ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን በአንድነት መፍታት አለብንም ብለዋል፡፡ ሰው በሰውነቱ እንጂ በብሔሩ መለካት እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከብልጽግና ፓርቲ መሪዎች ብዙ ሥራ ይጠበቃል ያሉት ሰልጣኙ፤ ለዘላቂ ሰላም በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ መሪዎች በአንድነት እንደተወያዩ ሁሉ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም ለአንድነት መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከመነቋቆር ይልቅ መመካከር፣ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን በማጎልበት የቀደመችውን ኢትዮጵያ ታሪክ በመጠበቅ ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል፡፡ አባቶች ለሀገር አንድነት እና መስዋትነት የከፈሉትን ዋጋ በልማት እና በእድገት መድገም ይገባል ነው ያሉት፡፡

በስልጠናው ራሳቸው እና ሌሎች ያሉበትን ደረጃ ለማየት እንዳበቃቸውም ገልጸዋል፡፡ ያለ ሰላም የሚተገበር ምንም ነገር አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡ ሁሉም ለሰላም በትኩረት መሥራት ይገባዋልም ብለዋል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር አለብንም ነው ያሉት፡፡ ራስ ወዳድ እና ሀገር የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችን መተው አለብንም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር የምትኾነው በአንድነት መሥራት ሲቻል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል የመጡት ሙሐሙድ መሐመድ ከብሔርተኝነት ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ከፍ ለማለት የሚያስችል የጋራ ስልጠና መውሰዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ተለያይቶ መኖር እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ አንዲት ጠንካራ ሀገር ኾና እንድትቀጥል የጋራ ሀሳቦች እና መግባባቶች ያስፈልጋሉም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አንዲት ናት፣ ወደፊትም አንዲት ኾና ትቀጥላለች፣ ተከባብሮ መኖር ብቻ ነው የሚያስፈልገን፣ ኢትዮጵያውያን ተለያይተው መኖር አይቻላቸውም ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር የጋራ ስልጠናዎች እና ውይይቶች ያስፈልጋሉም ብለዋል፡፡

ስለ አንድነት መወያየት እና በአንድነት መሥራት ይገባናል ነው ያሉት፡፡ በአንድነት መሥራት ከተቻለ ወደ ፊት ብዙ ተስፋዎች አሉም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር ለሰላም ዘብ መኾን ያስፈልጋል” ሠልጣኞች
Next article“የአማራ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደሚወራው አይደለም” የብልጽግና ፓርቲ ሰልጣኞች