
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥተው ባሕር ዳር የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች በባሕር ዳር ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር የሚገኙ ሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ እና ዓባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሀድያ ዞን እንደመጡ የነገሩን ሠልጣኝ እንዳሉት በባሕርዳር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከክልሉ አልፎ ለሀገር እድገት ሚናቸው የጎላ በመኾኑ ወደ ሙሉ ማምረት እንዲገቡ ለሰላም ሁሉም በጋራ መሥራት ይጠይቃል።
ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር ብዝሐነትን መቀበል እና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ፤ የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ በሕዝብ ኀላፊነት የተሰጠው አመራር ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሠራም አንስተዋል። መንግሥትም የሚነሱ የሕዝብን ጥያቄዎች መለየትና መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ጉጅ እንደመጡ የነገሩን ተሳታፊም ባሕርዳር ውብና የሰላም ከተማ መኾኗን ገልጸው በባሕርዳር እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አቅም ፈጥሯል ብለዋል። ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሰከነ መንገድ መወያየት መደማመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በሥልጠናው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የብልጽግና ፓርቲ የሥልጠና ተሳታፊዎች መገኘት ደግሞ ሕብረ ብሔራዊነትን ያጎለብታል፤ አንዱ የአንዱን ችግር ተረድቶ የመፍትሔ አካል እንዲኾን ያግዛል ነው ያሉት።
ከድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የተገኙት ተሳታፊም በባሕርዳር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማስቀጠል ኅብረተሰቡ ለሀገር ሰላም ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት። ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል። ለሰላም ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!