“ባሕር ዳር በልማት ጎዳና ላይ የምትገኝ ጽዱ ከተማ ናት” የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች

45

ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሁሉም ክልሎች የተሰባሰቡ በባሕር ዳር ከተማ “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል ርእስ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ ሥልጠና ተሳታፊዎች የከተማውዋን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና የኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝታቸው ዘመናዊውን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ፣ የከተማዋን የመንገድ ዳርቻ መዝናኛዎችን እና የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ተመልክተዋል።

ሠልጣኞቹ ባሕር ዳር ከተማ በልማት ጎዳና ላይ የምትገኝ ጽዱ ከተማ ስለመኾኗ ተናግረዋል።

ከተማዋ የሀገር ኢኮኖሚን ከመገንባት በተጨማሪ በርካታ ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ትላልቅ ፋብሪካዎች ያሏት ስለመኾኑም አንስተዋል።

በከተማዋ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ ትላልቅ የዘይት ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን ተጠቅመው የሚያመርቱ በመኾናቸው ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል፡፡ በተለይም ክልሉ በቅባት እህሎች ምርት ትልቅ አቅም ያለው በመኾኑ ለሀገር የሚበቃ የዘይት ምርት ለማግኘት እንደሚያስችልም የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

የልማት እንቅስቅሴውን የተመለከቱት የሥልጠናው ተሳታፊዎች በከተማዋ የሚገኘውን ግዙፍ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካንም ተመልክተዋል።

ፋብሪካው ኢትዮጵያ ያላትን የእንሳት ሃብት የበለጠ በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን አጋዥ ነውም ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ የመንገድ ዳርቻዎች እና የመዝናኛ ቦታዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅም ስለመኾናቸውም ተነስቷል። ባሕርዳር ጽዱ ከተማ በመኾኗ እና ነዋሪዎቿም እንግዳ ተቀባዮች በመኾናቸው በቱሪስቶች ተመራጭ ያደርጋታል ነው ያሉት።

ባሕርዳር የዘመናዊ ኢንዱስትሪ መንደር ባለቤት መኾኗን ስለመመልከታቸውም ተናግረዋል። በቂ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማምረት እና የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማጽናት የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም በምልከታቸው ላይ ያነጋገርናቸው የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሐ ግብር እንዲጠናቀቁ እና ሀገራዊ አንድነት እንዲጸና ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ነው” የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች
Next articleየ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አካል የኾኑ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።