“የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሐ ግብር እንዲጠናቀቁ እና ሀገራዊ አንድነት እንዲጸና ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ነው” የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች

23

ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተሰባስበው በባሕር ዳር ከተማ ሥልጠና ላይ ናቸው። ከቀናት በፊት ወደ ከተማዋ ገብተው ሥልጠና የጀመሩት የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች በዛሬው ውሏቸው በከተማዋ በመንግሥት እና ባለሃብቶች እየተገነቡ ያሉ የልማት እና መሠረተ ልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።

በመጀመሪያው ጉብኝታቸው በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ ድልድይ የተመለከቱት ሠልጣኞች በቀጣይም በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ በባለሃብቶች የሚገነባውን ጣና ማሪና ባሕር ዳርን ተመልክተዋል።

ባሕር ዳር የተለየ ተፈጥሯዊ ውበት የተሰጣት ከተማ ናት የሚሉት ሠልጣኞቹ መንግሥት እና ባለሃብቶች እያደረጉት ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ያደርጋታል ነው ያሉት።

ሕብረ ብሔራዊቷ ኢትዮጵያ እርስ በእርሳቸው የሚመጋገቡ እና የሚስማሙ ጸጋዎች አሏት ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ጸጋዎችን በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም ተቀራርቦ መነጋገር እና አንዱ ሌላውን መረዳት አለበት ብለዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ሥልጠና ላይ ያለው የብልጸግና መሪዎች ታናሿን ኢትዮጵያ የሚመስል ነው፡፡ በባሕር ዳር ያየውን ጸጋ፣ የማኅበረሰቡ እንግዳ ተቀባይነት እና የሕዝቡን ፍቅር ለሌላው ኅብረተሰብ በማድረስ የጋራ እውነት መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሐ ግብር እንዲጠናቀቁ ፣ ሀገራዊ አንድነት እንዲጸና እና የተጀመረው ሀገራዊ እድገት ዘላቂ እንዲኾን ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል ሠልጣኞቹ።

የልዩነት ሃሳብ ያለው ሁሉ ከአፈሙዝ ይልቅ ንግግርን ቁልፍ የችግሮች መፍቻ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። ባሕር ዳር ከሌሎች የሀገሪቷ ከተሞች ጋር ያላትን ቅርርብ እና ትስስር እንድታጠናክር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰልጣኞች አዲሱን የዓባይ ድልድይ እየጎበኙ ነው።
Next article“ባሕር ዳር በልማት ጎዳና ላይ የምትገኝ ጽዱ ከተማ ናት” የብልጽግና ፓርቲ ሠልጣኞች