
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወባ በሽታ በክረምት መግቢያ እና መውጫ ጊዜያት በስፋት ይከሰታል። በሽታው ቀድሞ ህክምና ካላገኘ ደግሞ ሞትን የሚያስከትል ነው። በተለይም አጎበርን በትክክል የማይጠቀሙ ፣ረግረጋማ አካባቢዎች እና ውኃ ባቆሩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎችን በስፋት ያጠቃል። በዚህ ዓመት በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ ወባ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የወባ በሽታ ሥርጭቱ በስፋት ተከስቶ በርካቶችን ለህመም ዳርጓል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር የጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ እጸገነት አምላክ እንደነገሩን በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም ብልጫ አለው፡፡ ለበሽታው መጨመር አጎበርን በትክክል አለመጠቀም፣ ያቆሩ ቦታዎችን አለማፋሰስ እና ለወባ ትንኝ መራባት አመች የኾነ የአየር ጸባይ መኖር በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ ምክትል ኀላፊዋ የወባ በሽታ መመርመሪያ ኪት በአግባቡ ለጤና ተቋማቱ አለመድረስ እና ሌሎች ግብአቶች በወቅታዊ ችግር ምክንያት መቅረብ አለመቻላቸው በሽታው የበለጠ እንዲሰፋ ማድረጉን አስረድተዋል። የወባ በሽታ በዞኑ 24 በመቶ እንደጨመረ ገልጸው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት ከጤና ተቋም ወደ ጤና ተቋም እንዲዋዋሱ እየተደረገ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
በክልሉ በኩል በሽታውን ለመከላከል አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የወባ ስርጭት በሚበዛባቸው ሊቦ ከምከም ወረዳ ላይ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰዎች ፣ፎገራ ወረዳ 1ሺህ 86 ሰዎች፣ ደራ ወረዳ 651 ሰዎች እና ወረታ ከተማ ላይ 606 ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ነው ያስረዱት ምክትል ኀላፊዋ፡፡ በዞኑ የተከሰተውን የወባ በሽታ ስርጭት ለማቆም ሁሉም ሰው ለወባ ወረርሽኝ የሚያጋልጡ አካባቢዎችን በማጽዳት ፣አጎበርን በተገቢው በመጠቀም እና የወባ መድኃኒት መረጨት ያለባቸው አካባቢዎች እንዲረጩ በማድረግ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!