
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ በ2015 ክረምት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ አዳዲስ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህን ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ እና ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ማኅበረሰቡ መንከባከብ እንዳለበት ክልሉ አሳስቧል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 376 ሚሊዮን ችግኞች እንክብካቤ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት፡፡ ችግኞችን የመንከባከቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል፡፡ በሥራው ላይ 74 ሺህ 700 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውንም አንስተዋል፡፡
አቶ እስመለዓለም አሁን ላይ 85 በመቶ ያህል ችግኞች እንክብካቤ ማግኘት እንደነበረባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት በሚፈለገው መጠን ችግኞችን መንከባከብ አለመቻሉንም ያነሳሉ፡፡ እንዲኹም የመረጃ መለዋወጫ መንገዶች ዝግ መኾን ሌላው እንቅፋት እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በሰሜን ጎንደር እና በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ብቻ በአግባቡ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ችግኞችን የመንከባከቡ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ችግኞችን መንከባከብ የኅልውና ጉዳይ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
የተተከለውን ችግኝ በእኔነት ሥሜት መንከባከብ ጉዝጓዝ ማልበስ፣ በቀጣይ ሰብል ሲነሳም ለእንስሳት እንዳይጋለጡ ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በየአካባቢው በግለሰብ እና በቡድን የተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ማኅበራዊ ኀላፊነትን መወጣት እንደሚገባም ጠቁዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!