“ትምህርት ወድቋል ለማለት የሚቀድመን የለም፤ ነገር ግን እኔ ለትምህርት ጥራት ምን አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ የሚል የለም” ተስፋዬ ሽፈራው (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ዙሪያ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ትውልዱ ግብረ ገብነት እንዳይኖረው ከማድረግ ጀምሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያልተማከለ ትምህርት ትውልድን ጎድቷል ሲባል ኖሯል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ በፈጠረው ክፍተት ኢትዮጵያ ያልተረጋጋ ሰላም እንዲኖራት፣ አንድነት እንዲቀንስ፣ ብሔራዊ ስሜት እንዲላላ እና በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዳይፈጠር ምክንያት ኾኗል የሚሉትም ብዙዎች ናቸው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ መዛባት ምክንያት ሀገር የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኀይል እና ከተማረ የሰው ኀይል የምታገኘውን ጥቅም አለማግኘቷም ይነገራል፡፡ ለዓመታት የዘለቀው ችግር ደግሞ በቅርቡ ውጤቱን አሳይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀውን ችግር ይቀንሳል የተባሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራለች፡፡ ለአብነት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ መልክ አስፈትናለች፡፡ በአዲስ መልክ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ደግሞ ለዓመታት የዘለቀውን ችግር እና የትምህርት ሥርዓቱ የመጣበትን እውነተኛ መንገድ አሳይቷል፡፡ አዲስ በተጀመረው የአፈታተን ሥርዓት ፈተናውን አልፈው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚገቡት ተማሪዎች ይልቅ ፈተናውን ሳያልፉ የሚቀሩት በእጅጉ ይልቃሉ፡፡ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው እየተባለ ቢነገርም “ውኃን ከጥሩ ነገርን ከሥሩ” እንዲሉ አበው ከሥሩ ጀምሮ መፍትሔ ካልተበጀለት ለዓመታት የዘለቀውን ችግር መፍታት አይቻልም የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቁርጠኝነት መሥራትና መፍትሔዎቹ ላይ መረባረብ ይገባል፡፡

የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ሽፈራው (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ለመጣው የትምህርት ስብራት እና የውጤት ማሽቆልቆል መፍትሔው ከንግግር ባለፈ ቁርጠኛ የኾነ ሥራ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ስለ ችግሩ መሸፋፈን መሞጋገስ አያስፈልግም፤ ችግሩን በደንብ አውጥቶ መፍትሔውንም በደንብ መፈለግ ግድ ይለናልም ብለዋል፡፡

የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሲሠራ አባል ኾነው መሥራታቸውን ያነሱት ዶክተር ተስፋዬ በክልሎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ነግረውናል። ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ወላጆች እና መሪዎችን አግኝተን አነጋግረናቸዋል፤ ችግሮችን ለይተን ጎን ለጎን የመፍትሔ ሀሳብም አስቀምጠን ነበር፡፡ ነገር ግን የተቀመጠውን መፍትሔ የሚተገብረው የለም ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ይሄን ቢያደርጉት ወይም ቢያደርገው ይላል እንጂ እኔ ይሄን ማድረግ አለብኝ ብሎ የሚነሳ ቁርጠኛ ሰው አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ወድቋል ለማለት የሚቀድመን የለም፣ ነገር ግን እኔ ለትምህርት ጥራት ምን አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ? ብሎ የሚጠይቅ ጠፍቷልም ብለዋል፡፡

በትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት ሁላችንም ተናጋሪዎች ሁነናል ለትምህርት ጥራትስ ምን ያክል ሁላችን ሠርተናል ብለን መጠየቅ ይገባናልም ብለዋል ዶክተር ተስፋዬ፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ የትምህርት ተቋሙን የሚመሩ መሪዎች ለትምህርት ጥራት ያደረኩት አስተዋጽዖ ምንድን ነው ? ብለው መጠየቅ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለትምህርት ጥራት አስተዋጽዖ ማድረግ ካልቻለ ችግሮችን መፍታት አይቻለንም ብለዋል፡፡ የትምህርት ስብራቱን ያመጡት ችግሮች እንደሚታወቁ የተናገሩት ዶክተር ተስፋዬ መትሔዎች ላይ መሥራት ግን አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ ትምህርት ቤት ሳይኖር ትምህርት ቤት አለ እያልን፣ ተማሪዎች ከማወቃቸው በላይ ማለፋቸው እና ከቁጥር አለመጉደላቸው እያስጨነቀን፣ ቁጥራቸው እንዳይጎድል ሁሉንም ማሳለፍ አለብን እያልን እንዴት ነው የትምህርት ጥራትን የምናረጋግጠው ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ያቋረጠ ተማሪ ከተማሪዎች መዝገብ ላይ በማይሰረዝበት ሥርዓት ውስጥ የትምህርት ጥራትን ማምጣት አይቻልምም ብለዋል፡፡ የትምህርት መሪዎች ከክፍል ክፍል የማይዘዋወሩ ተማሪዎችን አትቀንሱ እያሉ በሚያዝዙበት እና የጥራት ጉዳይ በማይታሰብበት ሂደት ውስጥ ጥራትን ማሰብ እና የተሻለ ውጤትን ማለም አዳጋች መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የተለመደው ምን ያክል ተማሪዎችን አብቅቻለሁ ሳይኾን ምን ያክል ተማሪዎችን ከክፍል ክፍል አዘዋውሬያለሁ የሚለው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ሳያውቁ ማለፍ የለባቸውም፣ ተማሪዎችም ሳናውቅ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አይገባንም እንዲሉ ማድረግ አለብንም ብለዋል፡፡ ለትምህርት ጥራቱ ሁሉም መረባረብ አለበት ነው ያሉት፡፡

ዪኒቨርሲቲዎች ያላቸውን እውቀት ወደ ታች አውርደው መተግበር ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ የእውቀት ሽግግር ማድረግና መማማር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች አላለፉም ብሎ ማልቀስ ሳይኾን አብረን ከኖርነው ችግር ጋር መላቀቅ ያስፈልገናል ነው ያሉት፡፡ ችግሮቻችን በቁርጠኝነት መፍታት እንጂ በችግሮቻችን ማልቀስ አይገባምም ብለዋል፡፡

ከስብዕና ግንባታ ጀምሮ ትምህርት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባናል ነው ያሉት፡፡ በጋራ መሥራት እንጂ በችግሮች ላይ በጋራ ማዘን አያስፈልግምም ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ላይ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች አዕምሯቸውን እንዲጠቀሙ እድል አለመሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ለተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍ ሳይሰጡ ተማሪዎች ሳያልፉ ቀሩ ብሎ ማዘን ልክ አይደለምም ብለዋል፡፡

ለችግሮቻችን እውቅና አልሰጠናቸውም የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ ከችግር ጋር መኖር ለእኛ የተፈቀደልን ለምንድን ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ለምንድን ነው ችግር ውስጥ እንድኖር የኾንኩት? ለምንድን ነው አቧራ በሞላው ትምህርት ቤት ውስጥ ተማር የተባልኩት? ብሎ መጠየቅና ለመፍትሔው በቁርጠኝነት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡ የተሟሉ ትምህርት ቤቶችን ሳይዙ ሳይንቲስቶች፣ ሐኪሞችና ፓይለቶች እንዲኾኑ መፈለግ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡ የሚፈልጉትን ለማግኘት የሚያስፈልገውን ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፣ ቁርጠኞች ከኾን ግን ችግሮቻችንን እንፈታቸዋን ነው ያሉት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጊዜያቸው ያለፈባቸው እና በአግባቡ ያልተቀመጡ መድኃኒቶች፣ ምግብ እና ምግብነክ ነገሮችን ላለመጠቀም ጥንቃቄ እንዲደረግ ጤና ቢሮ አሳሰበ፡፡
Next articleማኅበረሰቡ በየአካባቢው የሚገኙ የአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን እንዲንከባከብ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጠየቀ፡፡