ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና በአግባቡ ያልተቀመጡ መድኃኒቶች፣ ምግብ እና ምግብነክ ነገሮችን ላለመጠቀም ጥንቃቄ እንዲደረግ ጤና ቢሮ አሳሰበ፡፡

19

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መድኃኒቶች፣ ምግቦች እና ምግብ ነክ ነገሮች በአቀማመጥ ችግር እና በመጠቀሚያ ጊዜያቸው አገልግሎት ላይ ካልዋሉ ለብልሽት ይዳረጋሉ፡፡ እነዚህን መድኃኒቶች፣ ምግቦች እና ምግብ ነክ ነገሮች መጠቀም ደግሞ የጤና ጉዳት ያስከትላል፡፡

አቶ ባንቴ አንተነህ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቀበሌ 11 ነዋሪ ናቸው፡፡ በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርተው ኑሯቸውን ይመራሉ፡፡ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡትን ምግብ እና ምግብነክ ነገሮች ከዋና አከፋፋዮች ሲረከቡ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ የሚገዟቸውን ምግብ እና ምግብነክ ነገሮች የሚያስቀምጡበትን ቦታም መርጠው ነው፡፡ ምግብ እና ምግብነክ ጉዳዮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈ እና በአቀማመጥ ለብክለት ከተዳረጉ የተጠቃሚውን ጤና ለችግር እንደሚያጋልጡ በትምህርት ላይ በነበራቸው ቆይታ ተገንዝበዋል፡፡ በዚህም ለተጠቃሚዎች በሚያቀርቧቸው ምግብ እና ምግብነክ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ምግብ እና ምግብ ነክ ነገሮች በውስጠኛው ክፍል እና በውጭ ማሸጊያው ላይ የተቀመጠው የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ የተለያየ ኾኖ እንደሚገኝም ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች ውስጥ መኾናቸውን ያነሳሉ፡፡

አቶ በላይ ከፋለ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር የቀበሌ 14 ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ከፋለ እና ባለቤታቸው የጤና ባለሙያ ናቸው፡፡ ለልጆቻቸው ቤት ውስጥ የተዘጋጁ የአትክልት ጭማቂዎችን እንዲጠቀሙ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች እንደ ፓስታ፣ ማኮሮኒ እና የዳቦ ዱቄት የመሳሰሉ ምግቦችን ሲገዙ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ሃሳባቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ምግብ እና ምግብነክ ነገሮች ከአቀማመጥ ጉድለት፤ ከሚጓጓዙበት ሁኔታ ለብልሽት ሊዳረጉ ስለሚችሉ ግዥ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና እና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጌትነት ስንታየሁ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ነገሮች በፀሐይ፣ በቅዝቃዜ እና በሚቀመጡበት ቦታ ለብልሽት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል፡፡ እንዲኹም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦች ለገበያ የሚቀርቡበት ኹኔታ መኖሩንም አንስተዋል፡፡

ሥራው በተዋረድ በሚገኙ አካላት የሚሠራ ሲኾን በተለይ ጥቆማዎች ሲኖሩ ከክልል በሚደራጅ ቡድን ቁጥጥር እና ፍተሻ የሚያደረግበት አግባብ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ መድኃኒት አጠቃቀም ላይ ጉድለት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች፣ ምግብ እና ምግብነክ ነገሮች ሲገዛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ1ሺህ 800 በላይ የመድኃኒት የችርቻሮ መሸጫ መደብሮች፣ ከ530 በላይ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቷቸው አገልግሎት እየሠጡ ያሉ ባሕላዊ ሕክምና ተቋማት የቁጥጥሩ አካል መኾናችውን ጠቁመዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም በተደረገ ቁጥጥር ፡-
👉 ለ73 የመድኃኒት መቸርቸሪያ መደብሮች የቃል ማስጠንቀቂያ ተሠጥቷል፡፡
👉 ለ178 የምግብ እና ምግብ ነክ አቅራቢዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡
👉 28 የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች ታግደዋል፡፡
👉 22 የምግብ እና ምግብነክ ነገሮች መሸጫ መደብሮች ታግደዋል፡፡
👉 7 የመድኃኒት ችርቻሮ መሸጫ ሱቅ ንግድ ፈቃድ ተሰርዟል፡፡

በተካሄደ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ 760 ሺህ ብር የሚገመት በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ መድኃኒት እና 13 ሚሊዮን 836 ሺህ 494 ብር የሚገመት ምግብ እና ምግብነክ ጉዳዮች ከአገልግልት ውጭ ኾነው መወገዳቸውን አንስተዋል፡፡

የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው እና የተወገዱ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ የታሸጉ ምግቦችን ሲጠቀም የተመረቱበትን ቦታ፣ የተመረቱበት ቀን፣ ከአገልግሎት ውጭ የሚኾኑበትን ቀን በትክክል ማየት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

አቶ ጌትነት በቅቤ፣ ማር እና በርበሬ ላይ እየተጨመረ ያለው ባዕድ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ጠቁመዋል፡፡

ይኽንን ችግር ለመከላከል በጥቂት የሰው ኃይል መሸፈን እንደማይቻል ያነሱት ዳይሬክተሩ ማኅበረሰቡ ችግሩን ለመከላከል ተባባሪ እና የራሱን ጤና የሚጠብቅ መኾን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።
Next article“ትምህርት ወድቋል ለማለት የሚቀድመን የለም፤ ነገር ግን እኔ ለትምህርት ጥራት ምን አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ የሚል የለም” ተስፋዬ ሽፈራው (ዶ.ር)