
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት በድርቅ እና በግጭት ጉዳት የደረሰባቸዉ ወደ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸዉን አስታውቋል። በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸዉ አካባቢዎች የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በሠጠዉ መግለጫ አስታዉቋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ድኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ከሀምሌ 2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ድረስ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የሚተመን የገንዘብ ድጋፍ እና ከ798 ሺህ ኩንታል በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ መድረሱን ተናግረዋል። በዚህም ወደ 7 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። የስንዴ ዱቄት፣ አልሚ ምግቦች እና ሌሎችም ድጋፎች መደረጋቸዉንም አንስተዋል።
ድጋፉ የተደረገዉ በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልል በድርቅና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸዉ አካባቢዎች ነው ተብሏል። በተጨማሪም በጋምቤላም በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወደ 25 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ መደረጉን ነው ያነሱት፡፡
ዘጋቢ ፡- ኤልሳ ግዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!