“የቅርሶች መጎዳት የማኅበረሰቡ እሴት፣ ባሕል እና ሥነ- ልቦና እንደመጎዳት ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

27

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በርካታ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና የአርኪዮሎጅ ቅርሶች የሚገኙበት አካባቢ ነው። እነዚህ ቅርሶች በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ መንገድ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ ነግረውናል። በተለይም ደግሞ የማኅበረሰብ ማንነት መገለጫ የኾኑ ቅርሶች በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነትም ኾን ተብሎ ጭምር ዘረፋ የተፈጸመባቸው ቅርሶች መኖራቸውን የደሴ ሙዚየምን በማሳያነት አንስተዋል። በበጀት ችግር ክልሉ ካለው የቅርስ መጠን ልክ ማከናወን ባይቻልም በክልሉ መንግሥትና በፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

በ2015 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት በመደበው 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር 32 የቅርስ ማዕከላትን እና የሙዚየም ግንባታ ሥራን በማሳያነት አንስተዋል። በ2016 በጀት ዓመት ቢሮው ለቅርስ ጥገናና እንክብካቤ የሚኾን 300 ሚሊዮን ብር በላይ የክልሉን መንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ከሚያከናውነው የቅርስ እንክብካቤ ባለፈ የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንም ዓለም አቀፍ ቅርሶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ለማሳያነትም የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና አንስተዋል፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጥናቱ ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል ተብሏል።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዓለም አቀፍ ቅርሶች ባለፈ ከክልሉ አቅም በላይ የኾኑ ቅርሶችንም ከቢሮው ጋር በመተባበር የጥገናና እንክብካቤ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኡራ ኪዳነ ምህረት እና አዝዋ ማርያም፣ ላስታ አካባቢ ከላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጋር አቻ የኾኑ ሶስት ቅርሶች እና ሌሎችም ቅርሶችን የጥገናና እንክብካቤ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ለአብነት አንስተዋል።

የአንድ ቅርስ መጎዳት የማኅበረሰቡን እሴት፣ ባሕል፣ ሥነ ልቦና ጭምር መጉዳት በመኾኑ ማንኛውም የክልል ነዋሪ ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ማሻሻል ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
Next article“7 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች አስቸካይ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት