
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ስር ከሚገኙ 66 ሺህ ሠራተኞች መካከል 41 ሺህ የሚኾኑት የጤና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሰው ሃብት ልማቱ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሰው ሃብት ልማት ቡድን መሪ የሻነው አስናቀ ቢሮው የዓለም ጤና ድርጅት የሃኪም ለሕዝብ ጥምርታ መስፈርትን ለማሟላት ሥልጠናዎችን እየሰጠ ነው ብለዋል። በ23 የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች የሚሰጠው ሥልጠና የሐኪሞችን ቁጥር ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል። አቶ አስናቀ ከአጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች ውስጥ 65 በመቶ የሚኾኑት የትምህርት ዝግጅታቸው ዲፕሎማ ነው ብለዋል። እነዚህን ባለሙያዎች ወደ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ ለማሳደግ እየተሠራ ቢኾንም በቂ ግን አይደለም ብለዋል። የጤና ባለሙያዎችን አቅም በትምህርት ለማሳደግ ያለው አሠራር ፈጣን እና ኮታው የጨመረ መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
አቶ የሻነው “የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ማሻሻል ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል። በመኾኑም በአማራ ክልል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ጭምር በላቀ ትኩረት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!