
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተሻሉ ተቋማት የተሻሉ ትውልዶችን ይሰጣሉ፣ የእውቀት ማዕከላት በእውቀት ያደጉ ልጆችን ያፈራሉ፣ ለሀገር ተስፋ የኾኑ የሀገር ልጆችን ያሳያሉ፡፡ መልካም ዘርን የዘራ መልካምን ያጭዳል፣ መልካም ፍሬንም ያገኛል፡፡ መጥፎ ዘርንም የዘራ እንደ ዘሩ ያገኛል፡፡ ብዙዎች ለሀገራቸው እድገት ታላላቅ ተቋማትን ይገነባሉ፣ ተቋማቱ የሀገራቸውን ታሪክ የሚመጥን፣ ዘመኑን የዋጀ፣ የሚመጣውን ዘመንም ታሳቢ ያደረገ እንዲኾን ያደርጋሉ፡፡ በጠንካራ ተቋማታቸው ጠንካራ ሥርዓት እየዘረጉ በፈተና የማትደናቀፍ ሀገር ይፈጥራሉ፡፡ ለችግሮቻቸውም ሳይቸገሩ መፍትሔዎችን ይሰጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ እንደ አዲስ በተጀመረው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እስካሁን ያልተለመዱ ውጤቶች ታይተዋል፡፡ ብዙዎች ተደናግጠዋል፡፡ ብዙዎች ተከፍተዋል፡፡ ብዙዎችም ሥርዓቱን ሲወቅሱ ታይተዋል፡፡ ሊመጣ የሚችለውን በማሰብ አስቀድመው የሠሩ ተቋማት ደግሞ ሁሉንም ያሳዘነው እና ያስደነገጠው ችግር ሳይገጥማቸው ፈተናዎችን በድል ተወጥተዋል፡፡ ፈተናዎችን ከተወጣው ተቋም መካከል ደግሞ የባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል አንዱ ነው፡፡
የባሕዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ሽፈራው (ዶ.ር) የባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ትውልድን ለመቅረጽ ታስቦ የተቋቋመ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ተቋም ምሥጋና ይግባቸውና በበጎ አድራጊው በማርክ ጌልፋንድ አማካኝነት የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ ማርክ ጌልፋንድ ለሳይንስ በነበራቸው ፍቅር በባሕርዳር የእውቀት ማዕከል እንዲገነባ አደረጉ፡፡ ከዓመታት በፊት ማዕከሉ ሲቋቋም የራሳቸውን ወጪ አውጥተው ተቋሙን ገነቡ፡፡ በራሳቸው ወጪ፣ በራሳቸው ባለሙያዎች አስገንብተውም ለባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አስረከቡት፡፡ እኒህ በጎ ፈቃደኛ ሰው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለሳይንስ ያላቸውን ፍቅር እና ያላቸውን ችሎታ ተመልክተው ነበር ማዕከሉን ያስገነቡ ዘንድ የወደዱት፡፡
ማዕከሉ በውስጡ የተሻሉ ቤተ ሙከራዎች አሉት፣ በመጀመሪያ አካባቢ ተማሪዎች አዳዲስ የፕሮጄክት ሀሳቦች ሲኖሯቸው እያቀረቡ፣ መምህራን እየተመደቡላቸው ይሠሩበት እንደነበር ዶክተር ተስፋዬ ያስታውሳሉ፡፡ ልጆችን ሳይንስን በቀልድ መልክ እንዲማሩ እያደረጉ፣ እንዲፈላሰፉ፣ እንዲጠይቁ፣ ለምን ይሄ ኾነ ? እያሉ እንዲሞግቱ የማድረግ ሥራ ማሥራታቸውንም ነግረውናል፡፡
ለእያንዳንዱ ነገር ይጠይቃሉ፣ የኾነው ሁሉ ለምን ኾነ ይላሉ፡፡ ተማሪዎች አዳዲስ ነገሮችን ይሞክራሉ፣ በአዳዲስ ጉዳዮችም ይፈላሰፋሉ፡፡ ማዕከሉ በርከት ያሉ ፕሮጄክቶችን ይሞክራል፣ ወላጆችን ያሳትፋል፣ ጠንካራ ውድድሮችን ያካሂዳል፣ ሮኬቶችን ሁሉ እስከማስወንጨፍ ደርሷል፡፡ በማዕከሉ ቴክኖሎጂዎችን ሲሞክሩ የነበሩ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ዪኒቨርሲቲዎች የመማር እድል አግኝተው መማራቸውን እና አንዳንዶችም በዛው ለማስተማር መቅረታቸውን ነው የገለጹት፡፡ በማዕከሉ የወጡ ተማሪዎች ሰፋፊ እድሎችን እያገኙ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከውጭ የሚመጡ አሰልጣኞች የልጆችን አቅም እያዩ እድሎችን እያመቻቹላቸው መኾናቸውን እና በእድሉም ተጠቃሚ የኾኑ ተማሪዎች አሉ ነው ያሉት፡፡
“የመጀመራችን ዋናው ዓላማ ለምን ብሎ የሚጠይቅ፣ ሳይንስን የሚፈትሽ፣ ለችግሮች መፍቻነት የሚያውል ትውልድ ለመፍጠር ነው” ብለውናል፡፡ በማዕከሉ የተፈተኑ ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናን ሳያልፉ ቀርተው እንደማያውቁም ገልጸዋል፡፡ የማዕከሉ ተማሪዎች አንድን ፈተና ከማለፍ ባሻገር ያሉ እውቀቶችን እንደሚገበዩ እና ሰፋ ያለ እውቀት ያላቸው ልጆች መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዝም ብሎ ፈተና እንዲያልፉ ብቻ ሳይኾን እውቀት በውስጣቸው እንዲኖር ይደረጋል ነው ያሉን፡፡ በውስጥ የሰረጸ እውቀት አንድን ፈተና ተፈትኖ ከማለፍ ባሻገር ነውና፡፡ ተማሪዎቻቸው ከፈተና ባሻገር ያለውን እንዲያውቁ፣ የነገ የሀገር ተረካቢ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የሕክምና ሊሕቃን እንዲኾኑ እንደሚያደርጓቸው እና ለሀገር አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ልጆችን የመፍጠር እቅድ ይዘው እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡ “የእውነት የሚጠይቁ፣ የእውነት የሚመልሱ፣ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ ልጆችን ለማውጣት ነው ያቋቋምነው” ብለዋል፡፡
መምህራን በልጆቹ ላይ ያለውን ተስፋ እያዩ የተሻለ እውቀት ይሰጧቸዋል፣ ልጆቹም ጠያቂዎች ናቸው ተብሏል፡፡ ማዕከሉ በጥሩ ጉዞ ላይ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ በስቲም ማዕከሉ የተማሩ ተማሪዎች ወደ ዪኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች የቀደመ እውቀት እንደሚይዙም ገልጸ ዋል፡፡ ልጆቹን ሊመጥን የሚችል ዪኒቨርሲቲ እንደ ሀገር መቋቋም እንዳለበትም ዶክተር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ተስፋ ሰጪ እውቀት ያላቸው፣ ሀገር ወደፊት ተስፋ የምታደርግባቸው ልጆች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የተሻለ ትምህርት አግኝተው ለሀገሪቱ የተሻለ አቅም መኾን እንዲችሉ የማድረግ እሳቤ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ የልጆችን እውቀት ማባከን እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡ ቢቻል በውጭ ሀገራት ዪኒቨርሲቲዎች ተምረው እንዲመጡና ለሀገር እንዲጠቅሙ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የተሻለ ውጤት ለማምጣት የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ ተግባራዊ የኾኑ ትምህርቶችን ማስተማር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ሳይንስን ከሕይወታቸው ጋር እያቆራኙ እንዲማሩት እና እንዲያውቁት ማድረግ ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡ ያለውን ሀብት መጠቀም፣ ልጆችን እና መምህራንን ማብቃት ይገባልም ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ባወቁ ቁጥር ይጠይቃሉ፣ በጠየቁ ቁጥር ያውቃሉ፣ ለችግሮቻችንም መፍትሔዎችን ይዘው ይመጣሉ፣ ተማሪዎች ወደቁ የሚባለው ጥራት ያለው ትምህርት ባለመሰጠቱ ነውም ብለዋል፡፡ በይድረስ ይድረስ ትምህርት ውጤታማ እንደማይኾንም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ሰው ኀላፊነት ወስዶ ከታች ጀምሮ በጥንካሬ መሥራት ከቻለ ለውጥ ይመጣልም ብለዋል፡፡ እውቀትን ለማሳደግ እና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ባለሀብቶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ የምርምር ተቋማት የሚያወጧቸውን የምርምር ውጤቶች በገንዘብ በመደገፍ ማበልጸግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ትምህርት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የባሕርዳር ስቲም ማዕከልን አንድ ሰው እንደገነቡት ያስታወሱት ዶክተር ተስፋዬ ባለሀብቶች ትምህርት ላይ ኢንቨሰት ማድረግ ቢችሉ ብቁ ትውልድ የሚፈራባቸውን በርካታ ተቋማትን መገንባት እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ በርካታ ተማሪዎችን በተሻሉ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር የተሻሉ ተቋማትን ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ የሚማሩ ተማሪዎች ማድረግ እንችላለን የሚል ሥነ ልቡና አዳብረዋልም ብለዋል፡፡ በተሻሉ ተቋማት ያሉ ተስፋዎችን ማስፋት እና መጠቀም ይገባል ብለዋል ዶክተር ተስፋዬ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!