ጥያቄ አለኝ ከሚል ማንኛውም አካል ጋር በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመወያየት መንግሥት በሩ ክፍት መኾኑ ተገለጸ።

243

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑካን ቡድን በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።

ልዑካኑ በጉብኝታቸው በከተማዋ በመንግሥት የተሠሩ የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎችንና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ሕዝብን በማስተባበር በፍጥነት ወደ ልማት መመለስ ይገባቸዋል ብለዋል።

አቶ አደም አያይዘውም በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኀይል ለመንጠቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በፈተናዎች ውስጥ ኾነን ልማት ማምጣት እንደሚቻል በባሕር ዳር የተሠሩ የሕዝብ መናፈሻዎች ምስክሮች ናቸው ብለዋል።

እርስ በእርስ በመጠፋፋት የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ አይቻልም ያሉት አቶ ተስፋዬ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ክልሉ ወደ ቀድሞ ሰላሙ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። ጥያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመወያየት መንግሥት በሩ ክፍት መኾኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተጀምረው በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን የተናገሩት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የልማት መሰረቱ ሰላም ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላም ከሌለ የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ሚስኵርም 30/2016 ዓ.ስ
Next article“ዓላማችን ለምን? የሚል ትውልድ መፍጠር ነው” የባሕዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ሽፈራው (ዶ.ር)