
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪኮስት አዘጋጅነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 13 እስከ የካቲት11/2024 እንደሚካሄድ መርሐ ግብር ወጥቶለታል። 24 ሀገራትም በስድስት ምድብ መደልደላቸው ይፋ ተደርጓል።
በምድብ ሦሥት ከተደለደሉት ሀገራት አንዷ የኾነችው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋች የኾነው ሳዲዮ ማኔ በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የተደለደሉት 24ቱ ሀገራት ምርጥ ተጫዋቾችን ያሰባሰቡ በመኾናቸው ብርቱ ፉክክርና ማራኪ ጨዋታ እናይበታለን ብሏል። በእኔ ግምገማ ሁሉም ሀገራት ለዋንጫው ተጠባቂ ናቸው ነዉ ያለው። በተለይ የእኔ ሀገር ያለችበት ምድብ ምርጥ የእግር ኳስ ጨዋታ የሚታይበት ይኾናል በማለት ነው ሳዲዮ ማኔ ለቢቢሲ ስፖርት የተናገረው።
የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ ዲዲዬር ድሮግባ ሀገሩ ኮትድቯር የተደለደለችበትን ምድብ አንድ “የሞት ምድብ” ብሎታል።በዚህ ምድብ ኮትድቯር፣ ናይጀሪያ ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው ተደልድለዋል።
በምድብ ሁለት ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን የወሰደችው ግብጽ፣ የአራት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ጋና፣ ኬፕ ቨርዴ እና ሞዛምቢክ ተደልድለዋል። በዚህ ምድብ ግብጽ ልትፈተን የምትችለው በጋና ብቻ እንደኾነ እየተነገረ ነው።
በምድብ አራት ከተደለደሉት አልጀሪያ ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሞሪታኒያ እና አንጎላ፤ አልጀሪያ እና ቡርኪናፋሶ ነጥረው ይወጣሉ የሚል ግምት ከወዲሁ በእግርኳስ ተንታኞች እየተሰጠ ነው።
በምድብ አምስት ከተመደቡት ሀገራት ለናሚቢያ እና ማሊ ዝቅተኛ ግምት ሲሰጣቸው ቱኒዚያ እና ደቡብ አፍሪካ ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ይኾናሉ። በምድብ ስድስት ሞሮኮን ልትፈትናት የምትችለው የ2012ቱን የአፍሪካ ዋንጫ በአስደናቂ ብቃት የወሰደችው ዛምቢያ እንደኾነች ቢቢሲ ጠቅሷል። ዛምቢያና ታንዛኒያ ግን በጊዜ ሊሸኙ ይችላሉ ሲል ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል።
በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ አንድ ኮትድቯር እና ናይጀሪያ ፣ ከምድብ ሁለት ግብጽ ፣ ከምድብ ሦሥት ሴኔጋልና ካሜሩን ፣ከምድብ አራት አልጀሪያ እንዲሁም ከምድብ ስድስት ሞሮኮ ከአሁናዊ አቋማቸው አንጻር ዋንጫ ሊወስዱ ይችላሉ በማለት ዲዲዬር ድሮግባ፣ ሞሐመድ ሳላህ፣ ሳዲዮ ማኔ እና ሚካኤል ግምታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!